Amharic Quran

89|1|በጎህ እምላለሁ፡፡
89|2|በዐሥር ሌሊቶችም፡፡
89|3|በጥንዱም በነጠላውም፡፡
89|4|በሌሊቱም በሚኼድ ጊዜ፡፡
89|5|በዚህ (መሓላ) ለባለ አእምሮ ታላቅ መሓላ አለበትን?
89|6|ጌታህ በዓድ እንዴት እንደ ሠራ አታውቅምን?
89|7|በኢረም በባለ ረዣዢሚቱ አዕማድ፡፡
89|8|በዚያች ብጤዋ በአገሮች ውስጥ ያልተፈጠረ በኾነችው፡፡
89|9|በሰሙድም በእነዚያ በሸለቆው ቋጥኝን የቆረጡ በኾኑት፡፡
89|10|በፈርዖንም ባለ ችካሎች በኾነው፡፡
89|11|በእነዚያ በአገሮች ላይ ግፍ የሠሩ፡፡
89|12|በእርሷም ውስጥ ጥፋትን ያበዙ በኾኑት (እንዴት እንደሠራ አታውቅምን?)
89|13|በእነርሱ ላይም ጌታህ የቅጣትን አለንጋ አወረደባቸው፡፡
89|14|ጌታህ በመጠባበቂያ ላይ ነውና፡፡
89|15|ሰውማ ጌታው በሞከረው ጊዜ፣ ባከበረውና ባጣቀመውም (ጊዜ) «ጌታዬ አከበረኝ (አበለጠኝ)» ይላል፡፡
89|16|በሞከረውና በእርሱ ላይ ሲሳዩን ባጠበበ ጊዜማ «ጌታዬ አሳነሰኝ» ይላል፡፡
89|17|ይከልከል፤ ይልቁንም የቲምን አታከብሩም፡፡
89|18|ድኻንም በማብላት ላይ አትታዘዙም፡፡
89|19|የውርስንም ገንዘብ የመሰብሰብን አበላል ትበላላችሁ፡፡
89|20|ገንዘብንም ብዙን መውደድ ትወዳላችሁ፡፡
89|21|ተዉ፤ ምድር ደጋግማ በተሰባበረች ጊዜ፤
89|22|መላእክትም ሰልፍ ሰልፍ ኾነው ጌታህ (ትዕዛዙ) በመጣ ጊዜ፤
89|23|ገሀነምም በዚያ ቀን በተመጣች ጊዜ በዚያ ቀን ሰው (ጥፋቱን) ይገነዘባል፡፡ መገንዘብም ለእርሱ ከየቱ?
89|24|«ዋ እኔ! ምነው በሕይወቴ (መልካምን ሥራ) ባስቀደምኩ ኖሮ» ይላል፡፡
89|25|በዚያ ቀንም የርሱን አቀጣጥ አንድም አይቀጣም፡፡
89|26|የእርሱንም አስተሳሰር አንድም አያስርም፡፡
89|27|(ለአመነች ነፍስም) «አንቺ የረካሺው ነፍስ ሆይ!
89|28|«ወዳጅ ተወዳጅ ኾነሽ ወደ ጌታሽ ተመለሺ፡፡
89|29|«በባሮቼም ውስጥ ግቢ፡፡
89|30|ገነቴንም ግቢ፤» (ትባላለች)፡፡

Pages ( 89 of 114 ): « Previous1 ... 8788 89 9091 ... 114Next »