Amharic Quran

32|1|አ.ለ.መ (አሊፍ ላም ሚም)፡፡
32|2|የመጽሐፉ መወረድ ጥርጥር የለበትም፡፡ ከዓለማት ጌታ ነው፡፡
32|3|ይልቁንም «ቀጠፈው» ይላሉን? አይደለም፡፡ እርሱ ከጌታህ ዘንድ የሆነ እውነት ነው፡፡ በእርሱ ከአንተ በፊት ከአስፈራሪ (ነቢይ) ያልመጣባቸውን ሕዝቦች ልታስፈራራበት (ያወረደልህ ነው)፡፡ እነርሱ ሊምመሩ ይከጀላልና፡፡
32|4|አላህ ያ ሰማያትንና ምድርን በመካከላቸውም ያለውን ሁሉ በስድስት ቀኖች ውስጥ የፈጠረ ከዚያም በዐርሹ ላይ (ስልጣኑ) የተደላደለ ነው፡፡ ከእርሱ ሌላ ለእናንተ ረዳትም አማላጅም ምንም የላችሁም፤ አትገሰጹምን?
32|5|ነገሩን ሁሉ ከሰማይ ወደ ምድር ያዘጋጃል፡፡ ከዚያም ከምትቆጥሩት (ዘመን) ልኩ ሺህ ዓመት በሆነ ቀን ውስጥ ወደርሱ ይወጣል (ይመለሳል)፡፡
32|6|ይህ (ይህንን የሠራው) ሩቁንም ቅርቡንም ሁሉ ዐዋቂው አሸናፊው፣ አዛኙ (ጌታ) ነው፡፡
32|7|ያ የፈጠረውን ነገር ሁሉ ያሳመረው የሰውንም ፍጥረት ከጭቃ የጀመረው ነው፡፡
32|8|ከዚያም ዘሮቹን ከተንጣለለ፣ ከደካማ ውሃ ያደረገ ነው፡፡
32|9|ከዚያም (ቅርጹን) አስተካከለው፡፡ በእርሱ ውስጥም ከመንፈሱ ነፋበት፤ (ነፍስ ዘራበት)፡፡ ለእናንተም ጆሮዎችን፣ ዓይኖችንና ልቦችንም አደረገላችሁ፡፡ በጣም ጥቂትን ብቻ ታመሰግናላችሁ፡፡
32|10|«በምድርም ውስጥ (በስብሰን) በጠፋን ጊዜ እኛ በአዲስ መፈጠር ውስጥ እንሆናለን?» አሉ፡፡ በእውነቱ እነርሱ በጌታቸው መገናኘት ከሓዲዎች ናቸው፡፡
32|11|«በእናንተ የተወከለው መልአከ ሞት ይገድላችኋል፡፡ ከዚያም ወደ ጌታችሁ ትመለሳላችሁ» በላቸው፡፡
32|12|አመጸኞችም በጌታቸው ዘንድ ራሶቻቸውን ያቀረቀሩ ሆነው «ጌታችን ሆይ! አየን፣ ሰማንም፡፡ መልካምን እንሠራለንና (ወደ ምድረ ዓለም) መልሰን፡፡ እኛ አረጋጋጮች ነን፡፡» (የሚሉ ሲሆኑ) ብታይ ኖሮ (አስደንጋጭን ነገር ታይ ነበር)፡፡
32|13|በሻንም ኖሮ ነፍስን ሁሉ ቅንነቷን (እምነቷን) በሰጠናት ነበር፡፡ ግን ገሀነምን ከአጋንንትና ከሰዎች የተሰበሰቡ ሆነው በእርግጥ እሞላለሁ ማለት ቃሉ ከእኔ ተረጋግጧል፡፡
32|14|ይህንንም ቀናችሁን መገናኘትን በመርሳታችሁ ምክንያት (ቅጣትን) ቅመሱ! እኛ ተውናችሁ፡፡ ትሠሩት በነበራችሁትም ጥፋት ዘውታሪን ቅጣት ቅመሱ (ይባላሉ)፡፡
32|15|በአንቀጾቻችን የሚያምኑት እነዚያ በእርሷ በተገሰጹ ጊዜ ሰጋጆች ሆነው የሚወድቁትና እነርሱም የማይኮሩ ሆነው በጌታቸው ምስጋና (ተጎናጽፈው) የሚያወድሱት ብቻ ናቸው፡፡
32|16|ጌታቸውን ለመፍራትና ለመከጀል የሚጠሩት ሆነው ጎኖቻቸው ከመጋደሚያ ስፍራዎች ይራራቃሉ፡፡ ከሰጠናቸውም (ጸጋ) ይለገሳሉ፡፡
32|17|ይሠሩትም በነበሩት ለመመንዳት ከዓይኖች መርጊያ ለእነርሱ የተደበቀላቸውን (ጸጋ) ማንኛይቱም ነፍስ አታውቅም፡፡
32|18|አማኝ የሆነ ሰው አመጸኛ እንደ ሆነ ሰው ነውን? አይስተካከሉም፡፡
32|19|እነዚያ ያመኑና መልካሞችን የሰሩማ ለእነርሱ ይሠሩት በነበሩት ምክንያት መስተንግዶ ሲሆኑ መኖሪያ ገነቶች አሏቸው፡፡
32|20|እነዚያ ያመጹትማ፤ መኖሪያቸው እሳት ናት፡፡ ከእርሷ መውጣትን በፈለጉ ቁጥር በእርሷ ውስጥ ይመለሳሉ፡፡ ለእነርሱም «ያንን በእርሱ ታስተባብሉበት የነበራችሁትን የእሳት ቅጣት ቅመሱ» ይባላሉ፡፡
32|21|ይመለሱ ዘንድም ከትልቁ ቅጣት በፊት (በዚህ ዓለም) ከትንሹ ቅጣት በእርግጥ እናቀምሳቸዋለን፡፡
32|22|በጌታውም አንቀጾች ከተገሰጸና ከዚያም ከተዋት ሰው ይበልጥ በደለኛ ማነው? (የለም)፤ እኛ ከተንኮለኞቹ ተበቃዮች ነን፡፡
32|23|ሙሳንም መጽሐፍን በእርግጥ ሰጠነው፡፡ እርሱን ከመገናኘትህም በመጠራጠር ውስጥ አትሁን፡፡ ለእስራኤል ልጆችም መሪ አደረግነው፡፡
32|24|በታገሱና በተዓምራቶቻችን የሚያረጋግጡ በሆኑም ጊዜ ከእነርሱ በትዕዛዛችን የሚመሩ መሪዎች አደረግን፡፡
32|25|ጌታህ እርሱ በዚያ በእርሱ ይለያዩበት በነበሩት ነገር በትንሣኤ ቀን በመካከላቸው (በፍርድ) ይለያል፡፡
32|26|ከክፍለ ዘመናት ሰዎች ብዙዎችን ያጠፋን መሆናችን በመኖሪያዎቻቸው የሚሄዱ ሲሆኑ ለእነርሱ አልተገለፀላቸውምን? በዚህ ውስጥ ምልክቶች አሉት፤ አይሰሙምን?
32|27|እኛ ውሃን ወደ ደረቅ ምድር የምንነዳ እንስሶቻቸውና ነፍሶቻቸው ከእርሱ የሚበሉለትንም አዝመራ በእርሱ የምናወጣ መኾናችንን አያዩምን? አይመለከቱምን?
32|28|«ከእውነተኞችም እንደሆናችሁ ይህ ፍርድ መቼ ነው?» ይላሉ፡፡
32|29|«በፍርድ ቀን እነዚያን የካዱትን ሰዎች እምነታቸው አይጠቅማቸውም፡፡ እነርሱም ጊዜን አይሰጡም፤» በላቸው፡፡
32|30|እነርሱንም ተዋቸው፡፡ ተጠባበቅም፤ እነርሱ ተጠባባቂዎች ናቸውና፡፡

Pages ( 32 of 114 ): « Previous1 ... 3031 32 3334 ... 114Next »