Amharic Quran

71|1|እኛ ኑሕን «ሕዝቦችህን አሳማሚ ቅጣት ሳይመጣባቸው በፊት አስጠንቅቅ በማለት ወደ ሕዝቦቹ ላክነው፡፡»
71|2|(እርሱም) አለ «ሕዝቦቼ ሆይ! እኔ ለእናንተ ገላጭ የኾንኩ አስጠንቃቂ ነኝ፡፡
71|3|«አላህን ተገዙት፣ ፍሩትም፣ ታዘዙኝም በማለት፤ (አስጠንቃቂ ነኝ)፡፡
71|4|«ለእናንተ ከኀጢኣቶቻችሁ ይምራልና፡፡ ወደተወሰነው ጊዜም ያቆያችኋል፡፡ የአላህ (የወሰነው) ጊዜ በመጣ ወቅት አይቆይም፡፡ የምታውቁት ብትኾኑ ኖሮ (በታዘዛችሁ ነበር)፡፡»
71|5|(ስለ ተቃወሙትም) «አለ ጌታዬ ሆይ! እኔ ሌሊትም ቀንም ሕዝቦቼን ጠራሁ፡፡
71|6|«ጥሪየም መሸሽን እንጅ ሌላ አልጨመረላቸውም፡፡
71|7|«እኔም ለእነርሱ ትምር ዘንድ (ወደ እምነት) በጠራኋቸው ቁጥር ጣቶቻቸውን በጆሮዎቻቸው ውስጥ አደረጉ፡፡ ልብሶቻቸውንም ተከናነቡ፡፡ (በመጥፎ ሥራቸው ላይ) ዘወተሩም፡፡ (ያለ ልክ) መኩራትንም ኮሩ፡፡
71|8|«ከዚያም እኔ በጩኸት ጠራኋቸው፡፡
71|9|«ከዚያም እኔ ለእነርሱ ገለጽኩ፡፡ ለእነርሱም መመስጠርን መሰጠርኩ
71|10|«አልኳቸውም፡- ጌታችሁን ምሕረትን ለምኑት፡፡ እርሱ በጣም መሐሪ ነውና፡፡
71|11|«በእናንተ ላይ ዝናምን ተከታታይ አድርጎ ይልካል፡፡
71|12|«በገንዘቦችና በልጆችም ይለግሰላችኋል፡፡ ለእናንተም አትክልቶችን ያደርግላችኋል፡፡ ለእናንተም ወንዞችን ያደርግላችኋል፡፡»
71|13|ለአላህ ልቅናን የማትሹት ለእናንተ ምን አላችሁ?
71|14|በልዩ ልዩ ኹኔታዎች በእርግጥ የፈጠራችሁ ሲኾን፡፡
71|15|አላህ ሰባትን ሰማያት አንዱ ካንዱ በላይ ሲኾን እንዴት እንደፈጠረ አታዩምን?
71|16|በውስጣቸውም ጨረቃን አብሪ አደረገ፡፡ ፀሐይንም ብርሃን አደረገ፡፡
71|17|አላህም ከምድር ማብቀልን አበቀላችሁ፡፡
71|18|ከዚያም በውስጧ ይመልሳችኋል፡፡ ማውጣትንም ያወጣችኋል፡፡
71|19|አላህም ምድርን ለእናንተ ምንጣፍ አደረጋት፡፡
71|20|ከእርሷ ሰፋፊዎችን መንገዶች ትገቡ ዘንድ፡፡
71|21|ኑሕ አለ፡- «ጌታዬ ሆይ! እነሱ አምመጹብኝ፡፡ ገንዘቡና ልጁም ከጥፋት በስተቀር ያልጨመረለትን ሰው ተከተሉ፡፡
71|22|«ታላቅንም ተንኮል የመከሩትን ሰዎች» (ተከተሉ)፡፡
71|23|አሉም «አምላኮቻችሁን አትተዉ፡፡ ወድንም፣ ሱዋዕንም፣ የጉሥንም፣ የዑቅንም ነስርንም አትተው፡፡
71|24|«በእርግጥም ብዙዎችን አሳሳቱ፡፡ ከሓዲዎችንም ጥመትን እንጅ ሌላን አትጨምርላቸው» (አለ)፡፡
71|25|በኀጢኣቶቻቸው ምክንያት ተሰጠሙ፡፡ እሳትንም እንዲገቡ ተደረጉ፡፡ ለእነርሱም ከአላህ ሌላ የኾኑ ረዳቶችን አላገኙም፡፡
71|26|ኑሕም አለ «ጌታዬ ሆይ! ከከሓዲዎቹ በምድር ላይ አንድንም አትተው፡፡
71|27|«አንተ ብትተዋቸው ባሮችህን ያሳስታሉና፡፡ ኀጢኣተኛ ከሓዲንም እንጅ ሌላን አይወልዱም፡፡
71|28|«ጌታዬ ሆይ! ለእኔም ለወላጆቼም ምእመን ኾኖ በቤቴ ለገባም ሰው ሁሉ ለምእመናንና ለምእምናትም ምሕረት አድርግ፡፡ ከሓዲዎችንም ከጥፋት በቀር አትጨምርላቸው፤» (አለ)፡፡

Pages ( 71 of 114 ): « Previous1 ... 6970 71 7273 ... 114Next »