Amharic Quran

50|1|ቀ (ቃፍ) በተከበረው ቁርኣን እምላለሁ (በሙሐመድ አላመኑም)፡፡
50|2|ይልቁንም ከነሱ ጎሳ የኾነ አስፈራሪ ስለ መጣላቸው ተደነቁ፡፡ ከሓዲዎቹም «ይህ አስደናቂ ነገር ነው» አሉ፡፡
50|3|«በሞትንና ዐፈር በኾን ጊዜ (እንመለሳለን?) ይህ ሩቅ የኾነ መመለስ ነው፤» (አሉ)፡፡
50|4|ከእነርሱ (አካል) ምድር የምታጎድለውን በእርግጥ ዐውቀናል፡፡ እኛም ዘንድ ጠባቂ መጽሐፍ አልለ፡፡
50|5|(አልተመለከቱም)፡፡ ይልቁንም በቁርኣን በመጣላቸው ጊዜ አስተባበሉ፡፡ እነርሱም በተማታ ነገር ውሰጥ ናቸው፡፡
50|6|ወደ ሰማይም ከበላያቸው ስትኾን ለእርሷ ምንም ቀዳዳዎች የሌሏት ኾና እንዴት እንደ ገነባናትና (በከዋክብት) እንዳጌጥናት አልተመለከቱምን?
50|7|ምድርንም ዘረጋናት፡፡ በእርሷም ውስጥ ጋራዎችን ጣልንባት፡፡ በውስጧም ከሚያስደስት ዓይነት ሁሉ አበቀልን፡፡
50|8|(ይህንን ያደረግነው) ተመላሽ ለኾነ ባሪያ ሁሉ ለማሳየትና ለማስገንዘብ ነው፡፡
50|9|ከሰማይም ብሩክን ውሃ አወረድን፡፡ በእርሱም አትክልቶችንና የሚታጨድን (አዝመራ) ፍሬ አበቀልን፡፡
50|10|ዘምባባንም ረዣዢም ለእርሷ የተደራረበ እንቡጥ ያላት ስትኾን (አበቀልን)፡፡
50|11|ለባሮቹ ሲሳይ ትኾን ዘንድ (አዘጋጀናት)፡፡ በእርሱም የሞተችን አገር ሕያው አደረግንበት፡፡ (ከመቃብር) መውጣትም እንደዚሁ ነው፡፡
50|12|ከእነርሱ በፊት የኑሕ ሕዝቦችና የረሰስ ሰዎች፤ ሰሙድም አስተባበሉ፡፡
50|13|ዓድም ፈርዖንም፤ የሉጥ ወንድሞችም፤
50|14|የአይከት ሰዎችም የቱብበዕ ሕዝቦችም ሁሉም መልከተኞቹን አስተባበሉ፡፡ ዛቻዬም ተረጋገጠባቸው፡፡
50|15|በፊተኛው መፍጠር ደከምን? በእውነቱ እነርሱ ከአዲስ መፍጠር በመጠራጠር ውስጥ ናቸው፡፡
50|16|ሰውንም ነፍሱ (በሐሳቡ) የምታጫውተውን የምናውቅ ስንኾን በእርግጥ ፈጠርነው፤ እኛም ከደም ጋኑ ጅማት ይበልጥ ወደርሱ ቅርብ ነን፡፡
50|17|ሁለቱ ቃል ተቀባዮች (መላእክት) ከቀኝና ከግራ ተቀማጮች ኾነው በሚቀበሉ ጊዜ (አስታውስ)፡፡
50|18|ከቃል ምንም አይናገርም በአጠገቡ ተጠባባቂና ዝግጁ የኾኑ (መላእክት) ያሉበት ቢኾን እንጅ፡፡
50|19|የሞትም መከራ እውነቱን ነገር ታመጣለች፡፡ (ሰው ሆይ)፡- «ይህ ያ ከርሱ ትሸሸው የነበርከው ነው» (ይባላል)፡፡
50|20|በቀንዱም ውስጥ ይንነፋል፡፡ ያ (ቀን) የዛቻው (መፈጸሚያ) ቀን ነው፡፡
50|21|ነፍስም ሁሉ ከእርሷ ጋር ነጂና መስካሪ ያለባት ኾና ትመጣለች፡፡
50|22|«ከዚህ ነገር በእርግጥ በዝንጋቴ ውስጥ ነበርክ፡፡ ሺፋንህንም ካንተ ላይ ገለጥንልህ፡፡ ስለዚህ ዛሬ ዓይንህ ስለታም ነው» (ይባላል)፡፡
50|23|ቁራኛውም (መልአክ) «ይህ ያ እኔ ዘንድ ያለው ቀራቢ ነው» ይላል፡፡
50|24|«ሞገደኛ ከሓዲን ሁሉ በገሀነም ውስጥ ጣሉ፡፡»
50|25|«ለበጎ ሥራ ከልካይ፣ በዳይ፣ ተጠራጣሪ የኾነን ሁሉ፤» (ጣሉ)፡፡
50|26|«ያንን ከአላህ ጋር ሌላን አምላክ ያደረገውን በብርቱ ቅጣት ውስጥ ጣሉት፤» (ይባላል)፡፡
50|27|ቁራኛው (ሰይጣን) «ጌታችን ሆይ! እኔ አላሳሳትኩትም፡፡ ግን (ራሱ) በሩቅ ስሕተት ውስጥ ነበር» ይላል፡፡
50|28|(አላህ) «ወደእናንተ ዛቻን በእርግጥ ያስቀደምኩ ስኾን እኔ ዘንድ አትጨቃጨቁ» ይላቸዋል፡፡
50|29|«ቃሉ እኔ ዘንድ አይለወጥም፡፡ እኔም ለባሮቼ ፈጽሞ በዳይ አይደለሁም» (ይላቸዋል)፡፡
50|30|ለገሀነም «ሞላሽን? የምንልበትንና ጭማሪ አለን? የምትልበትን ቀን» (አስጠንቅቃቸው)፡፡
50|31|ገነትም አላህን ለፈሩት እሩቅ ባልኾነ ስፍራ ትቅቀረባለች፡፡
50|32|«ይህ ወደ አላህ ተመላሽና (ሕግጋቱን) ጠባቂ ለኾነ ሁሉ የተቀጠራችሁት ነው» (ይባላሉ)፡፡
50|33|«አልረሕማንን በሩቁ ኾኖ ለፈራና በንጹሕ ልብ ለመጣ» (ትቅቀረባለች)፡፡
50|34|«በሰላም ግቧት ይህ የመዘውተሪያ ቀን ነው» (ይባላሉ)፡፡
50|35|ለነርሱ በውስጧ ሲኾኑ የሚሹት ሁሉ አልላቸው፡፡ እኛም ዘንድ ጭማሪ አልለ፡፡
50|36|ከእነርሱም (ከቁረይሾች) በፊት ከክፍለ ዘመናት ሕዝቦች ብዙዎችን እነርሱ በኀያልነት ከእነርሱ ይበልጥ የበረቱ የኾኑትን (ማምለጫ ፍለጋ) በየአገሮቹም የመረመሩትን አጥፍተናል፡፡ ማምለጫ አለን?
50|37|በዚህ ውሰጥ ለእርሱ ልብ ላለው ወይም እርሱ (በልቡ) የተጣደ ኾኖ (ወደሚነበብለት) ጆሮውን ለጣለ ሰው ግሳጼ አለበት፡፡
50|38|ሰማያትንና ምድርን በመካከላቸው ያለውንም ሁሉ በስድስት ቀናት ውስጥ በእርግጥ ፈጠርን፡፡ ድካምም ምንም አልነካንም፡፡
50|39|በሚሉትም ላይ ታገሥ፤ ጌታህንም ከማመስገን ጋር ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት ከመግባቷም በፊት አወድሰው፡፡
50|40|ከሌሊቱም አወድሰው ከስግደቶችም በኋላዎች (አወድሰው)፡፡
50|41|(የሚነገርህን) አዳምጥም፡፡ ጠሪው ከቅርብ ስፍራ በሚጠራበት ቀን (ከመቃብራቸው ይወጣሉ)፡፡
50|42|ጩኸቲቱን በእውነት የሚሰሙበት ቀን ያ (ከመቃብር) የመውጫው ቀን ነው፡፡
50|43|እኛ እኛው ሕያው እናደርጋለን፡፡ እንገድላለንም፡፡ መመለሻም ወደእኛ ብቻ ነው፡፡
50|44|የሚፈጥኑ ኾነው ምድር ከእነርሱ ላይ የምትሰነጣጠቅበት ቀን (የመውጫው ቀን ነው)፡፡ ይህ በእኛ ላይ ገር የኾነ መሰብሰብ ነው፡፡
50|45|እኛ የሚሉትን ሁሉ ዐዋቂ ነን፡፡ አንተም በእነርሱ ላይ አስገዳጅ አይደለህም፡፡ ስለዚህ ዛቻየን የሚፈራን ሰው በቁርኣን አስታውስ፡፡

Pages ( 50 of 114 ): « Previous1 ... 4849 50 5152 ... 114Next »