Amharic Quran

52|1|በጡር (ጋራ) እምላለሁ፡፡
52|2|በተጻፈው መጽሐፍም፡፡
52|3|በተዘረጋ ብራና ላይ፤ (በተጻፈው)፡፡
52|4|በደመቀው ቤትም፡፡
52|5|ከፍ በተደረገው ጣራም፡፡
52|6|በተመላው ባሕርም እምላለሁ፡፡
52|7|የጌታህ ቅጣት በእርግጥ ወዳቂ ነው፤ (የማይቀር ነው)፡፡
52|8|ለእርሱ ምንም ገፍታሪ የለውም፡፡
52|9|ሰማይ ብርቱ መዞርን በምትዞርበት ቀን (ይኾናል)፡፡
52|10|ተራራዎችም መኼድን በሚኼዱበት (ቀን)፡፡
52|11|ለአስተባባዮችም ያን ጊዜ ወዮላቸው፡፡
52|12|ለእነዚያ እነርሱ በውሸት ውስጥ የሚጫወቱ ለኾኑት፡፡
52|13|ወደ ገሀነም እሳት በኀይል መግገፍተርን በሚግገፈተሩበት ቀን፡፡
52|14|ይህቺ ያቺ በእርሷ ታስተባብሉባት የነበራችሁት እሳት ናት፡፡
52|15|ይህ (ፊት ትሉ እንደነበራችሁት) ድግምት ነውን? ወይስ እናንተ አታዩምን?
52|16|ግቧት ታገሱም ወይም አትታገሡ በእናንተ ላይ እኩል ነው፡፡ የምትምመነዱት ትሠሩት የነበራችሁትን (ፍዳ) ብቻ ነው (ይባላሉ)፡፡
52|17|አላህን ፈሪዎቹ በእርግጥ በገነቶችና በጸጋ ውስጥ ናቸው፡፡
52|18|ጌታቸው በሰጣቸው ጸጋ ተደሳቾች ኾነው (በገነት ውስጥ ናቸው)፡፡ የገሀነምንም ስቃይ ጌታቸው ጠበቃቸው፡፡
52|19|«ትሠሩት በነበራችሁት ምክንያት ተደሳቾች ኾናችሁ ብሉ፤ ጠጡም፤» (ይባላሉ)፡፡
52|20|በተደረደሩ አልጋዎች ላይ ተደጋፊዎች ኾነው (በገነት ይኖራሉ)፡፡ ዓይናማዎች በኾኑ ነጫጭ ሴቶችም እናጠናዳቸዋለን፡፡
52|21|እነዚያም ያመኑትና ዝርያቸውም በእምነት የተከተለቻቸው ዝርያቸውን በእነርሱ እናስጠጋለን፡፡ ከሥራቸውም ምንም አናጎድልባቸውም፡፡ ሰው ሁሉ በሠራው ሥራ ተያዢ ነው፡፡
52|22|ከሚሹትም ሁሉ እሸትንና ስጋን እንጨምርላቸዋለን፡፡
52|23|በውስጧ መጠጥን ይሰጣጣሉ፡፡ በውስጧ ውድቅ ንግግርና መውወንጀልም የለም፡፡
52|24|ለነርሱም የኾኑ ወጣቶች ልክ የተሸፈነ ሉል መስለው በእነርሱ ላይ (ለማሳለፍ) ይዘዋወራሉ፡፡
52|25|የሚጠያየቁ ኾነውም ከፊላቸው በከፊሉ ላይ ይዞራል፡፡
52|26|«እኛ ፊት በቤተሰቦቻችን ውስጥ (ከቅጣት) ፈሪዎች ነበርን» ይላሉ፡፡
52|27|«አላህም በእኛ ላይ ለገሰ፡፡ የመርዛም እሳት ቅጣትንም ጠበቀን፡፡
52|28|«እኛ ከዚህ በፊት እንለምነው ነበርን፡፡ እነሆ እርሱ በጎ ዋይ አዛኝ ነውና» (ይላሉ)፡፡
52|29|(ሰዎችን) አስታውስም፡፡ አንተም በጌታህ ጸጋ ምክንያት ጠንቋይም ዕብድም አይደለህም፡፡
52|30|ይልቁንም የሞትን አደጋ በእርሱ የምንጠባበቅበት የኾነ ባለ ቅኔ ነው ይላሉን?
52|31|«ተጠባበቁ፤ እኔም ከእናንተ ጋር ከሚጠባበቁት ነኝ» በላቸው፡፡
52|32|አእምሮዎቻቸው በዚህ ያዟቸዋልን? አይደለም በእውነቱ እነርሱ ወሰን አላፊዎች ሕዝቦች ናቸው፡፡
52|33|ወይም «ቀጠፈው ይላሉን?» አይደለም፤ በእውነቱ አያምኑም፡፡
52|34|እውነተኞችም ቢኾኑ መሰሉ የኾነን ንግግር ያምጡ፡፡
52|35|ወይስ ያለ አንዳች (ፈጣሪ) ተፈጠሩን? ወይስ እነርሱ ፈጣሪዎች ናቸውን?
52|36|ወይስ ሰማያትንና ምድርን ፈጠሩን? አይደለም አያረጋግጡም፡፡
52|37|ወይስ የጌታህ ግምጃ ቤቶች እነርሱ ዘንድ ናቸውን? ወይስ እነርሱ አሸናፊዎች ናቸውን?
52|38|ወይስ ለእነርሱ በእርሱ ላይ (ከሰማይ) የሚያዳምጡበት መሰላል አላቸውን? አድማጫቸውም (ሰማሁ ቢል) ግልጽን አስረጅ ያምጣ፡፡
52|39|ወይስ ለእርሱ ሴቶች ልጆች አሉትን? ለእናንተም ወንዶች ልጆች አሏችሁን?
52|40|ወይስ ዋጋን ትጠይቃቸዋለህን? ስለዚህ እነርሱ ከዕዳው የተከበዱ ናቸውን?
52|41|ወይስ ሩቁ ምስጢር እነርሱ ዘንድ ነውን? ስለዚህ እነርሱ ይጽፋሉን?
52|42|ወይስ ተንኮልን (ባንተ) ይሻሉን? እነዚያም የካዱት እነርሱ በተንኮል ተሸናፊዎች ናቸው፡፡
52|43|ወይስ ለእነርሱ ከአላህ ሌላ አምላክ አላቸውን? አላህ ከሚያጋሩት ሁሉ ጠራ፡፡
52|44|ከሰማይም ቁራጭን (በእነርሱ ላይ) ወዳቂ ኾኖ ቢያዩ ኖሮ «ይህ የተደራረበ ደመና ነው» ይሉ ነበር፡፡
52|45|ያንንም በእርሱ የሚግገደሉበትን ቀናቸውን እስከሚገናኙ ድረስ ተዋቸው፡፡
52|46|ተንኮላቸው ከእነርሱ ምንንም የማይጠቅማቸውንና እነርሱም የማይርረዱበትን ቀን (እስከ ሚገናኙ ተዋቸው)፡፡
52|47|ለእነዚያ ለበደሉትም ከዚህ ሌላ ቅርብ ቅጣት አልላቸው፡፡ ግን አብዛኛዎቻቸው አያውቁም፡፡
52|48|ለጌታህ ፍርድም ታገሥ፡፡ አንተ በጥበቃችን ውስጥ ነህና፡፡ ጌታህንም በምትነሳ ጊዜ ከማመስገን ጋር አወድሰው፡፡
52|49|ከሌሊቱም አወድሰው፡፡ በከዋክብት መዳበቂያ ጊዜም (ንጋት ላይ አወድሰው)፡፡

Pages ( 52 of 114 ): « Previous1 ... 5051 52 5354 ... 114Next »