Amharic Quran

26|1|ጠ.ሰ.መ. (ጧ ሲን ሚም)፡፡
26|2|ይህች ግልጽ ከኾነው መጽሐፍ አንቀጾች ናት፡፡
26|3|አማኞች ባለመኾናቸው፤ (በቁጭት) ነፍስህን ገዳይ መኾን ይፈራልሃል፡፡
26|4|ብንሻ በእነሱ ላይ ከሰማይ ተዓምረን እናወርድና አንገቶቻቸው (መሪዎቻቸው) ለእርሷ ተዋራጆች ይኾናሉ፡፡
26|5|ከአልረሕማንም ዘንድ ኣዲስ የተወረደ ቁርኣን አይመጣላቸውም፤ ከእርሱ የሚሸሹ ቢኾኑ እንጂ፡፡
26|6|በእርግጥም አስተባበሉ፡፡ የዚያም በእርሱ ይሳለቁበት የነበሩት ወሬዎች (ፍጻሜ) ይመጣባቸዋል፡፡
26|7|ወደ ምድርም በውስጧ ከመልካም (በቃይ) ጎሳ ሁሉ ብዙን እንዳበቀልን አላዩምን፡፡
26|8|በዚህ አስደናቂ ምልክት አልለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም አማኞች አልነበሩም፡፡
26|9|ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊ አዛኝ ነው፡፡
26|10|ጌታህም ሙሳን «ወደ በደለኞቹ ሕዝቦች ኺድ» በማለት በጠራው ጊዜ (አስታውስ)፡፡
26|11|«ወደ ፈርዖን ሕዝቦች (ኺድ) አላህን አይፈሩምን» (አለው)፡፡
26|12|(ሙሳም) አለ «ጌታዬ ሆይ! እኔ ሊያስተባብሉኝ እፈራለሁ፡፡
26|13|«ልቤም ይጠብባል፡፡ ምላሴም አይፈታም፡፡ ስለዚህ ወደ ሃሩን ላክ፡፡
26|14|«ለእነርሱም በእኔ ላይ (የደም) ወንጀል አልለ፡፡ ስለዚህ እንዳይገድሉኝ እፈራለሁ፡፡»
26|15|(አላህ) አለ «ተው! (አይነኩህም)፡፡ በተዓምራቶቻችንም ኺዱ፡፡ እኛ ከእናንተ ጋር ሰሚዎች ነንና፡፡
26|16|«ወደ ፈርዖንም ኺዱ፡፡ በሉትም፡- እኛ የዓለማት ጌታ መልክተኞች ነን፡፡
26|17|«የእስራኤልን ልጆች ከእኛ ጋር ልቀቅ፡፡»
26|18|(ፈርዖንም) አለ «ልጅ ኾነህ በእኛ ውስጥ አላሳደግንህምን በእኛ ውስጥም ከዕድሜህ ብዙ ዓመታትን አልተቀመጥክምን
26|19|«ያችንም የሠራሃትን ሥራህን አልሠራህምን አንተም ከውለታ ቢሶቹ ነህ» (አለ)፡፡
26|20|(ሙሳም) አለ «ያን ጊዜ እኔም ከተሳሳቱት ኾኜ ሠራኋት፡፡
26|21|«በፈራኋችሁም ጊዜ ከእንናተ ሸሸሁ፡፡ ጌታየም ለእኔ ጥበብን ሰጠኝ፡፡ ከመልክተኞቹም አደረገኝ፡፡
26|22|«ይህችም የእስራኤልን ልጆች ባሪያ በማድረግህ በእኔ ላይ የምትመጻደቅባት ጸጋ ነት፡፡»
26|23|ፈርዖን አለ «(ላከኝ የምትለው) የዓለማትም ጌታ ምንድነው»
26|24|(ሙሳ) «የሰማያትና የምድር በመካከላቸውም ያለው ሁሉ ጌታ ነው፡፡ የምታረጋግጡ ብትኾኑ (ነገሩ ይህ ነው)፤» አለው፡፡
26|25|(ፈርዖንም) በዙሪያው ላሉት ሰዎች «አትሰሙምን» አለ፡፡
26|26|(ሙሳ) «ጌታችሁና የመጀመሪያዎቹ አባቶቻችሁም ጌታ ነው» አለው፡፡
26|27|(ፈርዖን) «ያ ወደእናንተ የተላከው መልክተኛችሁ በእርግጥ ዕብድ ነው» አለ፡፡
26|28|(ሙሳ) «የምሥራቅና የምዕራብ በመካከላቸውም ያለው ነገር ሁሉ ጌታ ነው፡፡ ታውቁ እንደኾናችሁ (እመኑበት)» አለው፡፡
26|29|(ፈርዖን) «ከእኔ ሌላ አምላክን ብትይዝ በውነቱ ከእስረኞቹ አደርግሃለሁ» አለ፡፡
26|30|(ሙሳ) «በግልጽ አስረጅ ብመጣህም እንኳ» አለው፡፡
26|31|«እንግዲያውስ ከእውነተኞች እንደኾንክ (አስረጁን) አምጣው» አለ፡፡
26|32|በትሩንም ጣለ፡፡ እርሷም ወዲያውኑ ግልጽ እባብ ኾነች፡፡
26|33|እጁንም አወጣ፡፡ ወዲያውም እርሷ ለተመልካቾች (የምታበራ) ነጭ ኾነች፡፡
26|34|(ፈርዖን) በዙሪያው ላሉት መማክርት «ይህ በእርግጥ ዐዋቂ ድግምተኛ ነው» አለ፡፡
26|35|«ከምድራችሁ በድግምቱ ሊያወጣችሁ ይፈልጋልና ምንን ታዛላችሁ» (አላቸው)፡፡
26|36|አሉት «እርሱን ወንድሙንም አቆይና በየከተሞቹ ሰብሳቢዎችን ላክ፡፡
26|37|«በጣም ዐዋቂ ድግምተኞችን ሁሉ ያመጡልሃልና፡፡»
26|38|ድግምተኞቹም በታወቀ ቀን ቀጠሮ ተሰበሰቡ፡፡
26|39|ለሰዎቹም «እናንተ ተሰብስባችኋልን» ተባለ፡፡
26|40|«ድግምተኞቹን እነሱ አሸናፊዎች ቢኾኑ እንከተል ዘንድ» (ተባለ)፡፡
26|41|«ድግምተኞቹም በመጡ ጊዜ ለፈርዖን እኛ አሸናፊዎች ብንሆን ለእኛ በእርግጥ ዋጋ አለን» አሉት፡፡
26|42|«አዎን፤ እናንተም ያን ጊዜ ከባለሟሎቹ ትኾናላችሁ» አላቸው፡፡
26|43|ሙሳ «ለእነርሱ እናንተ የምትጥሉትን ጣሉ» አላቸው፡፡
26|44|ገመዶቻቸውንና በትሮቻቸውንም ጣሉ፡፡ «በፈርዖንም ክብር ይኹንብን፡፡ እኛ በእርግጥ አሸናፊዎቹ እኛ ነን» አሉ፡፡
26|45|ሙሳም በትሩን ጣለ፡፡ ወዲያውም እርሷ የሚያስመስሉትን ሁሉ ትውጣለች፡፡
26|46|ድግምተኞቹም ሰጋጆች ኾነው ወደቁ፡፡
26|47|(እነሱም) አሉ «በዓለማት ጌታ አመንን፡፡
26|48|«በሙሳና በሃሩን ጌታ፡፡»
26|49|(ፈርዖንም) «ለእናንተ ሳልፈቅድላችሁ በፊት ለእርሱ አመናችሁን እርሱ ያ ድግምትን ያስተማራችሁ ታላቃችሁ ነው፡፡ ወደፊትም (የሚያገኛችሁን) በእርግጥ ታውቃላችሁ፡፡ እጆቻችሁንና እግሮቻችሁን (ቀኝና ግራን) በማናጋት እቆረርጣለሁ፡፡ ሁላችሁንም እሰቅላችኋለሁም» አለ፡፡
26|50|(እነርሱም) አሉ «ጉዳት የለብንም፡፡ እኛ ወደ ጌታችን ተመላሾች ነን፡፡
26|51|«እኛ የምእምናን መጀመሪያ በመኾናችን ጌታችን ኀጢአቶቻችንን ለእኛ ሊምር እንከጅላለን፡፡»
26|52|ወደ ሙሳም «ባሮቼን ይዘህ ሌሊት ኺድ፡፡ እናንተ የሚከተሉዋችሁ ናችሁና» ስንል ላክን፡፡
26|53|ፈርዖንም በየከተሞቹ ሰብሳቢዎችን (እንዲህ ሲል) ላከ፡፡
26|54|«እነዚህ ጥቂቶች ጭፈሮች ናቸው፡፡
26|55|«እነርሱም ለእኛ አስቆጪዎች ናቸው፡፡
26|56|«እኛም ብዙዎች ጥንቁቆች ነን፤» (አለ)፡፡
26|57|አወጣናቸውም፡፡ ከአትክልቶችና ከምንጮች፡፡
26|58|ከድልቦችም ከመልካም መቀመጫዎችም፡፡
26|59|እንደዚሁ ለእስራኤል ልጆች አወረስናትም፡፡
26|60|ፀሐይዋ ስትወጣም ተከተሉዋቸው፡፡
26|61|ሁለቱ ጭፍሮችም በተያዩ ጊዜ የሙሳ ጓዶች «እኛ(የፈርዖን ሰዎች) የሚደርሱብን ነን» አሉ፡፡
26|62|(ሙሳ) «ተዉዉ! ጌታዬ ከእኔ ጋር ነው፡፡ በእርግጥ ይመራኛል» አለ፡፡
26|63|ወደ ሙሳም «ባሕሩን በበትርህ ምታው» ስንል ላክንበት፡፡ (መታውና) ተከፈለም፡፡ ክፍሉም ሁሉ እንደ ታላቅ ጋራ ኾነ፡፡
26|64|እዚያም ዘንድ ሌሎችን አቀረብን፡፡
26|65|ሙሳንም ከእርሱ ገር ያሉትንም ሰዎች ሁሉንም አዳን፡፡
26|66|ከዚያም ሌሎቹን አሰጠምን፡፡
26|67|በዚህ ውስጥ ታላቅ ታምር አለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም አማኞች አልነበሩም፡፡
26|68|ጌታህም እርሱ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡
26|69|በእነሱም (በሕዝቦችህ) ላይ የኢብራሂምን ወሬ አንብብላቸው፡፡
26|70|ለአባቱና ለሕዝቦቹ «ምንን ትግገዛላችሁ» ባለ ጊዜ፡፡
26|71|«ጣዖታትን እንገዛለን፤ እርሷንም በመገዛት ላይ እንቆያለን» አሉ፡፡
26|72|(እርሱም) አለ «በጠራችኋቸው ጊዜ ይሰሟችኋልን
26|73|«ወይስ ይጠቅሟችኋልን ወይስ ይጎዷችኋልን»
26|74|«የለም! አባቶቻችን እንደዚሁ ሲሠሩ አገኘን» አሉት፡፡
26|75|«ትግገዙት የነበራችሁትን አስተዋላችሁን
26|76|«እናንተም የቀድሞዎቹ አባቶቻችሁም (የተግገዛችሁትን)፡፡»
26|77|«እነሱም (ጣዖቶቹ) ለእኔ ጠላቶች ናቸው፡፡ ግን የዓለማት ጌታ ሲቀር (እርሱ ወዳጄ ነው)፡፡
26|78|«(እርሱ) ያ የፈጠረኝ ነው፡፡ እርሱም ይመራኛል፡፡
26|79|«ያም እርሱ የሚያበላኝና የሚያጠጣኝ ነው፡፡
26|80|«በታመምኩም ጊዜ እርሱ ያሽረኛል፡፡
26|81|«ያም የሚገድለኝ ከዚያም ሕያው የሚያደርገኝ ነው፡፡
26|82|ያም በፍርዱ ቀን ኀጢአቴን ለእኔ ሊምር የምከጅለው ነው፡፡
26|83|ጌታዬ ሆይ! ዕውቀትን ስጠኝ! በደጋጎቹም ሰዎች አስጠጋኝ፡፡
26|84|በኋለኞቹም ሕዝቦች ውስጥ ለእኔ መልካም ዝናን አድርግልኝ፡፡
26|85|የጸጋይቱን ገነት ከሚወርሱትም አድርገኝ፡፡
26|86|ለአባቴም ማር፡፡ እርሱ ከተሳሳቱት ነበረና፡፡
26|87|በሚቀሰቀሱበት ቀንም አታዋርደኝ፡፡
26|88|ገንዘብም ልጆችም በማይጠቅሙበት ቀን፡፡
26|89|ወደ አላህ በንጹህ ልብ የመጣ ሰው ቢኾን እንጅ፡፡»
26|90|ገነትም ለፈሪዎች በምትቀረብበት (ቀን)፡፡
26|91|ገሀነምም ለጠመሞች በምትገለጽበት (ቀን)፡፡
26|92|ለእነሱም በሚባል ቀን «ትግገዟቸው የነበራችሁት የት ናቸው»
26|93|«ከአላህ ሌላ ሲኾኑ ይረዱዋችኋልን ወይስ (ለራሳቸው) ይርረዳሉን»
26|94|በውስጧም እነሱና ጠማሞቹ በፊቶቻቸው ተጥለው ይንከባለላሉ፡፡
26|95|የሰይጣንም ሰራዊቶች መላውም (ይጣላሉ)፡፡
26|96|እነርሱም በእርሷ ውስጥ የሚከራከሩ ኾነው ይላሉ፡-
26|97|በአላህ እንምላለን፤ እኛ በግልጽ መሳሳት ውስጥ ነበርን፡፡
26|98|(ጣዖቶቹን) በዓለማት ጌታ ባስተካከልናችሁ ጊዜ፡፡
26|99|አመጸኞቹም እንጅ ሌላ አላሳሳተንም፡፡
26|100|ከአማላጆችም ለእኛ ምንም የለንም፡፡
26|101|አዛኝ ወዳጂም (የለንም)፡፡
26|102|ለእኛም አንዲት ጊዜ መመለስ በኖረችንና ከአማኞቹ በኾን እንመኛለን (ይላሉ)፡፡
26|103|በዚህ ውስጥ አስደናቂ ግሳጼ አልለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም አማኞች አልነበሩም፡፡
26|104|ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡
26|105|የኑሕ ሕዝቦች መልክተኞችን አስተባበሉ፡፡
26|106|ወንድማቸው ኑሕ ለእነሱ ባላቸው ጊዜ «አትጠነቀቁምን
26|107|«እኔ ለእናንተ ታማኝ መልክተኛ ነኝ፡፡
26|108|«አላህንም ፍሩ ታዘዙኝም፡፡
26|109|«በእርሱም ላይ ምንም ዋጋ አልጠይቃችሁም፡፡ ዋጋዬ በዓለማት ጌታ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡
26|110|«አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡»
26|111|(እነርሱም) «ወራዶቹ የተከተሉህ ኾነህ ለአንተ እናምናለን» አሉት፡፡
26|112|(እርሱም) አላቸው «ይሠሩት በነበሩት ነገር ምን ዕውቀት አለኝ፡፡
26|113|«ምርመራቸው በጌታዬ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡ ብታውቁ ኖሮ (ይህንን ትርረዱ ነበር)፡፡
26|114|«እኔም አማኞችን አባራሪ አይደለሁም፡፡
26|115|«እኔ ግልጽ አስፈራሪ እንጅ ሌላ አይደለሁም፡፡»
26|116|«ኑሕ ሆይ! (ከምትለው) ባትከለከል በእርግጥ ከሚወገሩት ትኾናለህ» አሉት፡፡
26|117|(እርሱም) አለ «ጌታዬ ሆይ! ሕዝቦቼ አስተባበሉኝ፡፡
26|118|«በእኔና በእነርሱም መካከል (ተገቢ) ፍርድን ፍረድ፡፡ አድነኝም፡፡ ከእኔ ጋር ያሉትንም ምእምናን፡፡»
26|119|እርሱንም ከእርሱ ጋር ያለውንም ሁሉ በተመላው መርከብ ውስጥ አዳን፡፡
26|120|ከዚያም በኋላ ቀሪዎቹን አሰጠምን፡፡
26|121|በዚህ ውስጥ ታላቅ ግሳጼ አለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም አማኞች አልነበሩም፡፡
26|122|ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡
26|123|ዓድ መልክተኞችን አስተባበለች፡፡
26|124|ወንድማቸው ሁድ ለነርሱ ባላቸው ጊዜ «አትጠነቀቁምን
26|125|«እኔ ለናንተ ታማኝ መልክተኛ ነኝ፡፡
26|126|«አላህንም ፍሩ ታዘዙኝም፡፡
26|127|«በእርሱም ላይ ምንም ዋጋ አለምናችሁም፡፡ ዋጋዬ በዓለማት ጌታ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡
26|128|«የምትጫወቱ ኾናችሁ በከፍተኛ ስፍራ ሁሉ ላይ ምልክትን ትገነባላችሁን
26|129|«የውሃ ማጠራቀሚያዎችንና ሕንፃዎችንም ዘላለም መኖርን የምትከጅሉ ኾናችሁ ትሠራላችሁን
26|130|«በቀጣችሁም ጊዜ ጨካኞች ኾናችሁ ትቀጣላችሁን
26|131|«አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡
26|132|«ያንንም በምታውቁት (ጸጋ) ያጣቀማችሁን ፍሩ፡፡
26|133|«በእንስሳዎችና በልጆች ያጣቀማችሁን፡፡
26|134|«በአትክልቶችና በምንጮችም፡፡
26|135|«እኔ በእናንተ ላይ የታላቅን ቀን ቅጣት እፈራለሁና፡፡»
26|136|(እነርሱም) አሉ «ብትገስጽም ወይም ከገሳጮቹ ባትኾንም በእኛ ላይ እኩል ነው፤ (ያለንበትን አንለቅም)፡፡
26|137|«ይህ የፊተኞቹ ሰዎች ፀባይ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡
26|138|«እኛም የምንቅቀጣ አይደለንም» (አሉ)፡፡
26|139|አስተባበሉትም፡፡ አጠፋናቸውም፡፡ በዚህም ውስጥ እርግጠኛ ግሳጼ አለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም ምእመናን አልነበሩም፡፡
26|140|ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡
26|141|ሰሙድ መልክተኞችን አስተባበለች፡፡
26|142|ወንድማቸው ሷሊህ ለእነርሱ ባላቸው ጊዜ «አትጠነቀቁምን
26|143|«እኔ ለእናንተ ታማኝ መልክተኛ ነኝ፡፡
26|144|«አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡
26|145|«በእርሱም ላይ ምንም ዋጋ አልለምናችሁም፡፡ ዋጋዬ በዓለማት ጌታ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡
26|146|«በዚያ እዚህ ባለው (ጸጋ) ውስጥ የረካችሁ ኾናችሁ ትተዋላችሁን
26|147|«በአትክልቶችና በምንጮች ውስጥ፡፡
26|148|«በአዝመራዎችም ፍሬዋ የበሰለ በኾነች ዘንባባም፤ (ውስጥ ትተዋላችሁን)
26|149|«ብልሆች ኾናችሁ ከጋራዎች ቤቶችንም ትጠርባላችሁ፡፡
26|150|«አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡
26|151|«የወሰን አላፊዎችንም ትዕዛዝ አትከተሉ፡፡
26|152|«የእነዚያን በምድር ላይ የሚያጠፉትንና የማያበጁትን፡፡»
26|153|(እነሱም) አሉ «አንተ በብዙ ከተደገመባቸው ሰዎች ብቻ ነህ፡፡
26|154|«አንተ ብጤያችን ሰው እንጅ ሌላ አይደለህም፡፡ ከእውነተኞቹም እንደኾንክ ተዓምርን አምጣ፡፡»
26|155|(እርሱም) አለ «ይህች ግመል ናት፡፡ ለእርሷ የመጠጥ ፋንታ አላት፡፡ ለእናንተም የታወቀ ቀን ፋንታ አላችሁ፡፡
26|156|«በክፉም አትንኳት፡፡ የታላቅ ቀን ቅጣት ይይዛችኋልና፡፡»
26|157|ወጓትም፡፡ ወዲያውም ተጸጻቾች ኾነው አነጉ፡፡
26|158|ቅጣቱም ያዛቸው፡፡ በዚህም ውስጥ ግሳፄ አልለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም ምእመናን አልነበሩም፡፡
26|159|ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡
26|160|የሉጥ ሕዝቦች መልክተኞችን አስተባባሉ፡፡
26|161|ወንድማቸው ሉጥ ለእነርሱ ባለ ጊዜ «አትጠነቀቁምን
26|162|«እኔ ለእናንተ ታማኝ መልክተኛ ነኝ፡፡
26|163|«አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡
26|164|«በእርሱም ላይ ምንም ዋጋ አልለምናችሁም፡፡ ዋጋዬ በዓለማት ጌታ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡
26|165|«ከዓለማት ሰዎች ወንዶችን ትመጣላችሁን
26|166|«ከሚስቶቻችሁም ጌታችሁ ለናንተ የፈጠረላችሁን ትተዋላችሁን በእውነቱ እናንተ ወሰን አላፊዎች ሕዝቦ ናችሁ፡፡»
26|167|(እነርሱም) አሉ «ሉጥ ሆይ! ባትከለከል በእርግጥ (ከአገር) ከሚወጡት ትኾናለህ፡፡»
26|168|(እርሱም) አለ «እኔ ሥራችሁን ከሚጠሉት ሰዎች ነኝ፡፡
26|169|«ጌታዬ ሆይ! እኔንም ቤተሰቦቼንም ከሚሠሩት ሥራ (ቅጣት) አድነን፡፡»
26|170|እርሱንም ቤተሰቦቹንም በጠቅላላ አዳንናቸው፡፡
26|171|በቀሪዎቹ ውስጥ የኾነች አሮጊት ብቻ ስትቀር (እርሷ ጠፋች)፡፡
26|172|ከዚያም ሌሎቹን አጠፋን፡፡
26|173|በእነሱም ላይ (የድንጋይን) ዝናምን አዘነምንባቸው፡፡ የተስፈራሪዎቹም ዝናም (ምንኛ) ከፋ፡፡
26|174|በዚህ ውስጥ አስደናቂ ተዓምር አልለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም ምእመናን አልነበሩም፡፡
26|175|ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡
26|176|የአይከት ሰዎች መልክተኞችን አስተባበሉ፤
26|177|ሹዕይብ ለእነርሱ ባላቸው ጊዜ «አትጠነቀቁምን
26|178|«እኔ ለእናንተ ታማኝ መልክተኛ ነኝ፡፡
26|179|«አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡
26|180|«በርሱም ላይ ምንም ዋጋ አልጠይቃችሁም፡፡ ዋጋዬ በዓለማት ጌታ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡
26|181|«ስፍርን ሙሉ፡፡ ከአጉዳዮቹም አትኹኑ፡፡
26|182|«በትክክለኛ ሚዛንም መዝኑ፡፡
26|183|«ሰዎችንም ነገሮቻቸውን አታጉድሉባቸው፡፡ በምድርም ላይ አጥፊዎች ኾናችሁ አታበላሹ፡፡
26|184|«ያንንም የፈጠራችሁን የቀድሞዎቹንም ፍጡሮች (የፈጠረውን) ፍሩ፡፡»
26|185|አሉ «አንተ በብዛት ከተደገመባቸው ሰዎች ነህ፡፡
26|186|«አንተም ብጤያችን ሰው እንጅ ሌላ አይደለህም፡፡ እነሆ ከውሸታሞች ነህ ብለን እንጠረጥርሃለን፡፡
26|187|«ከእውነተኞቹም እንደኾንክ በእኛ ላይ ከሰማይ ቁራጭን ጣልብን፡፡»
26|188|«ጌታዬ የምትሠሩትን ሁሉ ዐዋቂ ነው፤» አላቸው፡፡
26|189|አስተባበሉትም፡፡ የጥላይቷ ቀን ቅጣትም ያዛቸው፡፡ እርሱ የከባድ ቀን ቅጣት ነበርና፡፡
26|190|በዚህ ውስጥ አስደናቂ ተዓምር አልለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም ምእምናን አልነበሩም፡፡
26|191|ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡
26|192|እርሱም (ቁርኣን) በእርግጥ ከዓለማት ጌታ የተወረደ ነው፡፡
26|193|እርሱን ታማኙ መንፈስ (ጂብሪል) አወረደው፤
26|194|ከአስፈራሪዎቹ (ነቢያት) ትኾን ዘንድ በልብህ ላይ (አወረደው)፡፡
26|195|ግልጽ በኾነ ዐረብኛ ቋንቋ፡፡
26|196|እርሱም (ቁርኣን) በቀድሞዎቹ መጻሐፍት ውስጥ (የተወሳ ነው)፡፡
26|197|የእስራኤል ልጆች ሊቃውንት የሚያውቁት መኾኑ ለእነርሱ (ለመካ ከሓዲዎች) ምልክት አይኾናቸውምን
26|198|ከአዕጀሞች ባንዱ ላይ ባወረድነውም ኖሮ፤
26|199|በእነርሱ ላይ ባነበበውም በእርሱ አማኞች አይኾኑም ነበር፡፡
26|200|እንደዚሁ (ማስተባበልን) በተንኮለኞች ልቦች ውስጥ አስገባነው፡፡
26|201|አሳማሚ ቅጣትን እስከሚያዩ ድረስ በእርሱ አያምኑም፡፡
26|202|እነርሱ የማያውቁ ሲኾኑ (ቅጣቱ) ድንገት እስከሚመጣባቸውም ድረስ (አያምኑም)፡፡
26|203|(በመጣባቸው ጊዜ) «እኛ የምንቆይ ነን» እስከሚሉም (አያምኑም)፡፡
26|204|በቅጣታችን ያቻኩላሉን
26|205|አየህን ብዙ ዓመታትን ብናጣቅማቸው፤
26|206|ከዚያም ያ ይስፈራሩበት የነበሩት ቢመጣባቸው፤
26|207|ይጣቀሙበት የነበሩት ሁሉ ከእነሱ ምንም አያብቃቃቸውም፡፡
26|208|አንዲትንም ከተማ ለእርሷ አስፈራሪዎች ያሏት (እና ያስተባበለች) ኾና እንጅ አላጠፋንም፡፡
26|209|(ይህች) ግሳፄ ናት፡፡ በዳዮችም አልነበርንም፡፡
26|210|ሰይጣናትም እርሱን (ቁርኣንን) አላወረዱትም፡፡
26|211|ለእነርሱም አይገባቸውም፤ አይችሉምም፡፡
26|212|እነርሱ (የመላእክትን ንግግር) ከመስማት ተከለከሉ ናቸው፡፡
26|213|ከአላህም ጋር ሌላን አምላክ አትግገዛ፤ ከሚቀጡት ትኾናለህና፡፡
26|214|ቅርቦች ዘመዶችህንም አስጠንቅቅ፡፡
26|215|ከምእምናንም ለተከተሉህ ሰዎች ክንፍህን ዝቅ አድርግ፤ (ልዝብ ኹን)፡፡
26|216|«እንቢ» ቢሉህም «እኔ ከምትሠሩት ንጹሕ ነኝ» በላቸው፡፡
26|217|አሸናፊ አዛኝ በኾነው (ጌታህ) ላይም ተጠጋ፡፡
26|218|በዚያ ለሶላት በምትቆም ጊዜ በሚያይህ፡፡
26|219|በሰጋጆች ውስጥ መዘዋወርህንም (በሚያየው ጌታህ ላይ ተጠጋ)፡፡
26|220|እነሆ እርሱ ሰሚው ዐዋቂው ነውና፡፡
26|221|ሰይጣናት በማን ላይ እንደሚወርዱ ልንገራችሁን
26|222|በውሸታም ኀጢአተኛ ሁሉ ላይ ይወርዳሉ፡፡
26|223|የሰሙትን (ወደ ጠንቋዮች) ይጥላሉ፡፡ አብዛኞቻቸውም ውሸታሞች ናቸው፡፡
26|224|ባለ ቅኔዎችንም ጠማማዎቹ ይከተሉዋቸዋል፡፡
26|225|እነርሱ በ(ንግግር) ሸለቆ ሁሉ የሚዋልሉ መኾናቸውን አታይምን
26|226|እነሱም የማይሠሩትን ነገር የሚናገሩ መኾናቸውን (አታይምን)፤
26|227|እነዚያ ያመኑና መልካም ሥራዎችን የሠሩ አላህንም በብዛት ያወሱ ከተበደሉም በኋላ (በቅኔ) የተከላከሉ ሲቀሩ፤ (እነርሱ አይወቀሱም)፡፡ እነዚያም የበደሉ (ከሞቱ በኋላ) እንዴት ያለን መመለስ እንደሚመለሱ በእርግጥ ያውቃሉ፡፡

Pages ( 26 of 114 ): « Previous1 ... 2425 26 2728 ... 114Next »