Amharic Quran

43|1|ሐ.መ (ሓ ሚም)፡፡
43|2|ገላጭ በኾነው መጽሐፍ እምላለሁ፡፡
43|3|እኛ ታውቁ ዘንድ ዐረብኛ ቁርኣን አደረግነው፡፡
43|4|እርሱም በመጽሐፎቹ እናት ውስጥ እኛ ዘንድ በእርግጥ ከፍተኛ ጥበብ የተመላ ነው፡፡
43|5|ድንበር አላፊዎች ሕዝቦች ለመኾናችሁ ቁርኣኑን ከእናንተ ማገድን እናግዳለን?
43|6|በፊተኞቹም ሕዝቦች ውስጥ ከነቢይ ብዙን ልከናል፡፡
43|7|ከነቢይም አንድም የሚመጣላቸው አልነበረም በእርሱ ይሳለቁበት የነበሩ ቢኾኑ እንጅ፡፡
43|8|ከእነርሱም በኀይል ይበልጥ የበረቱትን አጥፍተናል፡፡ የፊተኞቹም (አጠፋፍ) ምሳሌ አልፏል፡፡
43|9|«ሰማያትንና ምድርንም ማን ፈጠራቸው» ብለህ ብትጠይቃቸው «አሸናፊው ዐዋቂው (አላህ) በእርግጥ ፈጠራቸው» ይላሉ፡፡
43|10|(እርሱ) ያ ምድርን ለእናንተ ምንጣፍ ያደረገላችሁ በርሷም ውስጥ ትምመሩ ዘንድ ለእናንተ መንገዶችን ያደረገላችሁ ነው፡፡
43|11|ያም ከሰማያ ውሃን በልክ ያወረደላችሁ ነው፡፡ በእርሱም የሞተችውን አገር ሕያው አደረግን፡፡ እንደዚሁ (ከመቃብራችሁ) ትውወጣላችሁ፡፡
43|12|ያም ዓይነቶችን ሁሉ የፈጠረ ለእናንተም ከመርከቦችና ከቤት እንስሳዎች የምትጋልቧቸውን ያደረገላችሁ ነው፡፡
43|13|በጀርባዎቹ ላይ እንድትደላደሉ ከዚያም በርሱ ላይ የተደላደላችሁ ጊዜ የጌታችሁን ጸጋ እንድታስታውሱ፤ እንድትሉም፡- «ያ ይህንን የማንችለው ስንኾን ለእኛ ያገራለን ጌታ ጥራት ይገባው፡፡
43|14|እኛም በእርግጥ ወደ ጌታችን ተመላሾች፤ነን» (እንድትሉ)፡፡
43|15|ከባሮቹም ለእርሱ ቁራጭን (ልጅን) አደረጉለት፡፡ ሰው በእርግጥ ግልጽ ከሓዲ ነው፡፡
43|16|ከሚፈጥረው ውስጥ ሴቶች ልጆችን ያዘን? በወንዶች ልጆችም (እናንተን) መረጣችሁን?
43|17|አንዳቸውም ለአልረሕማን ምሳሌ ባደረገው ነገር (በሴት ልጅ) በተበሰረ ጊዜ እርሱ በቁጭት የተመላ ኾኖ ፊቱ የጠቆረ ይኾናል፡፡
43|18|በጌጥ (ተከልሶ) እንዲያድግ የሚደረገውን? እርሱም (ለደካማነቱ) በክርክር የሚያብራራውን ፍጡር (ሴትን) ለአላህ ያደርጋሉን?
43|19|መላእክትንም እነርሱ የአልረሕማን ባሮች የኾኑትን ሴቶች አደረጉ፡፡ ሲፈጠሩ ነበሩን? መመስከራቸው በእርግጥ ትጻፋለች፡፡ ይጠየቃሉም፡፡
43|20|«አልረሕማንም በሻ ኖሮ ባልተገዛናቸው ነበር» አሉ፡፡ ለእነርሱ በዚህ ምንም ዕውቀት የላቸውም፡፡ እነርሱ የሚዋሹ እንጅ ሌላ አይደሉም፡፡
43|21|ከእርሱ (ከቁርኣን) በፊት መጽሐፍን ሰጠናቸውን? ስለዚህ እነርሱ እርሱን የጨበጡ ናቸውን?
43|22|ከቶውንም «እኛ አባቶቻችንን በሃይማኖት ላይ አገኘናቸው፡፡ እኛም በፈለጎቻቸው ላይ ተመሪዎች ነን» አሉ፡፡
43|23|(ነገሩ) እንደዚሁም ነው፡፡ ከበፊትህ በማንኛይቱም ከተማ ውስጥ አስፈራሪን አልላክንም፤ ቅምጥሎችዋ እኛ አባቶቻችንን በሃይማኖት ላይ አገኘን፤ እኛም በፈለጎቻቸው ላይ ተከታዮች ነን ያሉ ቢኾኑ እንጅ፡፡
43|24|(አስፈራሪው) «አባቶቻችሁን በእርሱ ላይ ከአገኛችሁበት ይበልጥ ቀጥተኛን (ሃይማኖት) ባመጣላችሁም?» አላቸው፡፡ «እኛ በእርሱ በተላካችሁበት ነገር ከሓዲዎች ነን» አሉ፡፡
43|25|ከእነርሱም ተበቀልን፡፡ ያስተባባዮቹም መጨረሻ እንዴት እንደ ነበረ ተመልከት፡፡
43|26|ኢብራሂምም ለአባቱና ለሕዝቦቹ ባለ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ «እኔ ከምትግገዙት ሁሉ ንጹሕ ነኝ፡፡»
43|27|«ከዚያ ከፈጠረኝ በስተቀር (አልግገዛም)፡፡ እርሱ በእርግጥ ይመራኛልና፡፡»
43|28|በዝርዮቹም ውስጥ ይመለሱ ዘንድ (ባንድ አምላክ ማመንን) ቀሪ ቃል አደረጋት፡፡
43|29|ይልቅ እነዚህን (ቁረይሾችን)፣ አባቶቻቸውንም ቁርኣንና ገላጭ መልክተኛ እስከመጣላቸው ድረስ አጣቀምኳቸው፡፡
43|30|እውነቱም በመጣላቸው ጊዜ «ይህ ድግምት ነው፡፡ እኛም በእርሱ ከሓዲዎች ነን» አሉ፡፡
43|31|«ይህም ቁርኣን ከሁለቱ ከተሞች በታላቅ ሰው ላይ አይወረድም ኖሯልን?» አሉ፡፡
43|32|እነርሱ የጌታህን ችሮታ ያከፈፍላሉን? እኛ በቅርቢቱ ሕይወት ኑሯቸውን በመካከላቸው አከፋፍለናል፡፡ ከፊላቸውም ከፊሉን ሠራተኛ አድርጎ ይይዝ ዘንድ ከፊላቸውን ከከፊሉ በላይ በደረጃዎች (በሀብት) አበለጥን፡፡ የጌታህም ጸጋ (ገነት) ከሚሰበስቡት (ሃብት) በላጨ ናት፡፡
43|33|ሰዎችም (በክሕደት) አንድ ሕዝብ የሚኾኑ ባልነበሩ ኖሮ በአልረሕማን ፤ለሚክዱት ሰዎች (በዚህች ዓለም) ለቤቶቻቸው ከብር የኾኑን ጣራዎች በእነርሱ ላይ የሚወጡባቸውንም (የብር) መሰላሎች ባደረግንላቸው ነበር፡፡
43|34|ለቤቶቻቸውም ደጃፎችን በእነርሱ ላይ የሚደገፉባቸውንም አልጋዎች (ከብር ባደረግንላቸው ነበር)፡፡
43|35|የወርቅ ጌጥንም (ባደረግንላቸው ነበር)፡፡ ይህም ሁሉ የቅርቢቱ ሕይወት መጣቀሚያ እንጅ ሌላ አይደለም፤ (ጠፊ ነው)፡፡ መጨረሻይቱም አገር በጌታህ ዘንድ ለጥንቁቆቹ ናት፡፡
43|36|ከአልረሕማን ግሣጼ (ከቁርኣን) የሚደናበርም ሰው ለእርሱ ሰይጣንን እናስጠጋለን፡፡ ስለዚህ እርሱ ለእርሱ ቁራኛ ነው፡፡
43|37|እነርሱም (ተደናባሪዎቹ) ተመሪዎች መኾናቸውን የሚያስቡ ሲኾኑ እነርሱ (ሰይጣናት) ከቀጥተኛው መንገድ በእርግጥ ያግዷቸዋል፡፡
43|38|(በትንሣኤ) ወደኛ በመጣም ጊዜ (ቁራኛዬ ሆይ!) «በእኔና ባንተ መካከል የምሥራቅና የምዕራብ ርቀት በኖረ ወይ ምኞቴ! ምን የከፋህ ቁራኛ ነህ» ይላል፡፡
43|39|ስለ በደላችሁም ዛሬ እናንተ በቅጣት ተጋሪዎች መኾናችሁ አይጠቅማችሁም፤ (ይባላሉ)፡፡
43|40|አንተ ደንቆሮዎችን ታሰማለህን? ወይስ ዕውሮችንና በግልጽ ጥመት ውስጥ የኾኑን ሰዎች ትመራለህን?
43|41|አንተንም (ቅጣታቸውን ስታይ) ብንወስድህ እኛ ከእነርሱ ተበቃዮች ነን፡፡
43|42|ወይም ያንን የቀጠርናቸውን ብናሳይህ እኛ በእነርሱ (ቅጣት) ላይ ቻይዎች ነን፡፡
43|43|ያንንም ወደ አንተ የተወረደልህን አጥብቀህ ያዝ፡፡ አንተ በቀጥተኛው መንገድ ላይ ነህና፡፡
43|44|እርሱም (ቁርኣን) ለአንተ፣ ለሕዘቦችህም ታላቅ ክብር ነው፡፡ ወደ ፊትም (ከርሱ) ትጠየቃላችሁ፡፡
43|45|ከመልእክተኞቻችንም ካንተ በፊት የላክናቸውን (ተከታዮቻቸውን) ከአልረሕማን ሌላ የሚገዙዋቸው የኾኑን አማልክት አድርገን እንደ ኾነ ጠይቃቸው፡፡
43|46|ሙሳንም በተዓምራቶቻችን ወደ ፈርዖንና ወደ ሹማምንቶቹ በእርግጥ ላክን፡፡ «እኔ የዓለማት ጌታ መልክተኛ ነኝ» አላቸውም፡፡
43|47|በተዓምራታችንም በመጣባቸው ጊዜ ወዲያውኑ እነርሱ በእርሷ ይስቃሉ፡፡
43|48|ከተዓምርም አንዲትንም አናሳያቸውም እርሷ ከብጤዋ በጣም የበለጠች ብትኾን እንጅ፡፡ (ከክህደታቸው) ይመለሱም ዘንድ በቅጣት ያዝናቸው፡፡
43|49|«አንተ ድግምተኛ (ዐዋቂ) ሆይ! ጌታህን አንተ ዘንድ ቃል በገባልህ ለእኛ ለምንልን፡፡ እኛ (ቅጣቱን ቢያነሳልን) ተመሪዎች ነን» አሉም፡፡
43|50|ስቃዩን ከእነርሱ ላይ በገለጥንም ጊዜ ወዲያውኑ ኪዳናቸውን ያፈርሳሉ፡፡
43|51|ፈርዖንም በሕዝቦቹ ውስጥ ተጣራ፡፡ አለም፤ «ሕዝቦቼ ሆይ! የምስር ግዛት የኔ አይደለምን? እነዚህም ጅረቶች ከስሬ የሚፈሱ ሲኾኑ (የኔ አይደሉምን?) አትመለከቱምን?
43|52|«በውነቱ እኔ ከዚህ ያ እርሱ ወራዳ ንግግሩንም ሊገልጽ የማይቀርብ ከኾነው በላጭ ነኝ፡፡
43|53|«በእርሱም ላይ የወርቅ አንባሮች ለምን አልተጣሉበትም ወይም መላእክት ከእርሱ ጋር ተቆራኝተው ለምን አልመጡም» (አለ)፡፡
43|54|ሕዝቦቹንም አቄላቸው፡፡ ታዘዙትም፡፡ እነርሱ አመጸኞች ሕዝቦች ነበሩና፡፡
43|55|ባስቆጡንም ጊዜ ከእነርሱ በተበቀለን፡፡ ሁሉንም አሰጠምናቸውም፡፡
43|56|(በጥፋት) ቀዳሚዎችና ለኋለኞቹ (መቀጣጫ) ምሳሌም አደረግናቸው፡፡
43|57|የመርየም ልጅም ምሳሌ በተደረገ ጊዜ ሕዝቦችህ (ከሓዲዎቹ) ወዲያውኑ ከእርሱ ይስቃሉ፡፡
43|58|«አማልክቶቻችን ይበልጣሉን ወይስ እርሱ?» አሉም፡፡ ለክርክርም እንጅ ላንተ እርሱን ምሳሌ አላደረጉትም፡፡ በእውነት እነርሱ ክርክረ ብርቱ ሕዝቦች ናቸው፡፡
43|59|እርሱ በርሱ ላይ የለገስንለት ለእስራኤለም ልጆች ተዓምር ያደረግነው የኾነ ባሪያ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡
43|60|ብንሻም ኖሮ በምድር ላይ ከእናነተ ምትክ መላእክትን ባደረግን ነበር፡፡
43|61|እርሱም (ዒሳ) ለሰዓቲቱ (ማወቂያ) በእርግጥ ምልክት ነው፡፡ «በእርሷም አትጠራጠሩ፡፡ ተከተሉኝም፤ ይህ ቀጥተኛ መንገድ ነው» (በላቸው)፡፡
43|62|ሰይጣንም አያግዳችሁ፡፡ እርሱ ለእናንተ ግልጽ ጠላት ነውና፡፡
43|63|ዒሳ በታምራቶች በመጣ ጊዜም አላቸው «በእርግጥ በጥበብ መጣኋችሁ፡፡ የዚያንም በርሱ የምትለያዩበትን ከፊሉን ለናንተ ላብራራላችሁ (መጣሁ)፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ ታዘዙኝም፡፡
43|64|«አላህ ጌታዬ ጌታችሁም ነውና ተገዙት፡፡ ይህ ቀጥተኛ መንገድ ነው፡፡»
43|65|ከመካከላቸውም አሕዛቦቹ ተለያዩ፡፡ ለእነዚያም ለበደሉት ከአሳማሚ ቀን ቅጣት ወዮላቸው፡፡
43|66|ሰዓቲቱን እነርሱ የማያውቁ ኾነው በድንገት ልትመጣባቸው እንጅ ይጠባበቃሉን?
43|67|ወዳጆች በዚያ ቀን ከፊላቸው ለከፊሉ ጠላት ነው፡፡ አላህን ፈሪዎች ብቻ ሲቀሩ፡፡
43|68|(ለነርሱስ) «ባሮቼ ሆይ! ዛሬ ቀን በእናንተ ላይ ፍርሃት የለባችሁም እናንተም የምታዝኑ አይደላችሁም» (ይባላሉ)፡፡
43|69|እነዚያ በአንቀጾቻችን ያመኑና ፍጹም ታዛዦች የነበሩ (ባሮቼ ሆይ!)
43|70|«ገነትን ግቡ እናንተም ሚስቶቻችሁም ትደሰታላችሁ ትከበሩም አላችሁ» (ይባላሉ)፡፡
43|71|ከወርቅ የኾኑ ሰፋፊ ዝርግ ሳሕኖችና ኩባያዎች በእነርሱ ላይ ይዝዞራሉ፡፡ በእርሷም ውስጥ ነፍሶች የሚከጅሉት፣ ዓይኖችም የሚደሰቱበት ሁሉ አልለ፡፡ እናንተም በውስጧ ዘላለም ዘውታሪዎች ናችሁ፡፡
43|72|ይህችም ያቺ ትሠሩት በነበራችሁት ዋጋ የተሰጣችኋት ገነት ናት፡፡
43|73|ለእናንተ በውስጧ ብዙ ፍረፍሬዎች በእርግጥ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡
43|74|አመጸኞች በገሀነም ስቃይ ውስጥ በእርግጥ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡
43|75|ከእነርሱ (ቅጣቱ) አይቀለልላቸውም፡፡ እነርሱም በእርሱ ውስጥ ተሰፋ ቆራጮች ናቸው፡፡
43|76|አልበደልናቸውምም፤ ግን በዳዮቹ እነርሱው ነበሩ፡፡
43|77|«ማሊክ ሆይ! ጌታህ በኛ ላይ (በሞት) ይፍረድ፡፡» እያሉ ይጣራሉም፡፡ «እናንተ (በቅጣቱ ውስጥ) ዘላለም ነዋሪዎች ናችሁ» ይላቸዋል፡፡
43|78|እውነተኛውን መንገድ በእርግጥ አመጣንላችሁ፡፡ ግን አብዛኞቻችሁ እውነቱን ጠይዎች ናችሁ፡፡
43|79|ይልቁንም (በነቢዩ ላይ በማደም) ነገርን አጠነከሩን? እኛም (ተንኮላቸውን ወደእነርሱ በመመለስ) አጠንካሪዎች ነን፡፡
43|80|ወይም እኛ ምስጢራቸውንና ውይይታቸውን የማንሰማ መኾናችንን ያስባሉን? አይደለም፤ መልክተኞቻችንም እነርሱ ዘንድ ይጽፋሉ፡፡
43|81|«ለአልረሕማን ልጅ (የለውም እንጅ) ቢኖረው እኔ (ለልጁ) የተገዢዎቹ መጀመሪያ ነኝ» በላቸው፡፡
43|82|የሰማያትና የምድር ጌታ የዙፋኑ ጌታ ከሚሉት ነገር ሁሉ ጠራ፡፡
43|83|ተዋቸውም፡፡ ያንን ይስፈራሩበት የነበሩትን ቀናቸውን እስከሚገናኙ ድረስ (በስሕተታቸው ውስጥ) ይዋኙ ይጫዎቱም፡፡
43|84|እርሱም ያ በሰማይ ውስጥ ሊግገዙት የሚገባው በምድርም ውስጥ ሊግገዙት የሚገባው አምላክ ነው፡፡ እርሱም ብልሃተኛው ዐዋቂው ነው፡፡
43|85|ያም የሰማያትና የምድር በመካከላቸውም ያለው ሁሉ ንግሥና የእርሱ ብቻ የኾነው አምላክ ላቀ፡፡ የሰዓቲቱም (የመምጫዋ ዘመን) ዕውቀት እርሱ ዘንድ ብቻ ነው፡፡ ወደእርሱም ትመለሳላችሁ፡፡
43|86|እነዚያም ከአላህ ሌላ የሚግገዟቸው እነርሱ የሚያውቁ ኾነው በእውነት ከመሰከሩት በስተቀር ምልጃን አይችሉም፡፡
43|87|ማን እንደፈጠራቸውም ብትጠይቃቸው «በእርግጥ አላህ ነው» ይላሉ፡፡ ታዲያ (ከእምነት) ወዴት ይዞራሉ፡፡
43|88|(ነቢዩ) ጌታዬ ሆይ! እነዚህ የማያምኑ ሕዝቦች ናቸው፤ የማለቱም (ዕውቀት አላህ ዘንድ ነው)፡፡
43|89|እነርሱንም ተዋቸው፡፡ ነገሬ ሰላም ነው በልም፡፡ ወደፊትም (የሚመጣባቸውን) ያውቃሉ፡፡

Pages ( 43 of 114 ): « Previous1 ... 4142 43 4445 ... 114Next »