Amharic Quran

79|1|በኃይል አውጪዎች በኾኑት፤
79|2|በቀስታ መምዘዝንም መዘዦች በኾኑት፤
79|3|መዋኘትም ዋኚዎች በኾኑት፤
79|4|መቅደምንም ቀዳሚዎች በኾኑት፤
79|5|ነገርንም አስተናባሪዎች በኾኑት (መላእክት) እምላለሁ፡፡ (በእርግጥ ትቀሰቀሳላችሁ)፡፡
79|6|ተርገፍጋፊይቱ (ምድር) በምትርገፈገፍበት ቀን፤
79|7|ለጣቂይቱ የምትከተላት ስትኾን (ትቀሰቀሳላችሁ)፡፡
79|8|በዚያ ቀን ልቦች ተሸባሪዎች ናቸው፡፡
79|9|ዓይኖቻቸው ተዋራጆች (አቀርቃሪዎች) ናቸው፡፡
79|10|«እኛ ወደ መጀመሪያይቱ ኹነታ ተመላሾች ነን?» ይላሉ፡፡
79|11|«የበሰበሱ አጥንቶች በኾን ጊዜ (እንቀሰቀሳለን?)»
79|12|«ይህቺ ያን ጊዜ ባለ ከሳራ መመለስ ናት» ይላሉ፡፡
79|13|እርሷም አንዲት ጩኸት ብቻ ናት፡፡
79|14|ወዲያውኑም እነርሱ እንቅልፍ በሌለባት (ምድር) ላይ ይኾናሉ፡፡
79|15|የሙሳ ወሬ መጣልህን?
79|16|ጌታው በተቀደሰው ሸለቆ በጡዋ በጠራው ጊዜ፤
79|17|ወደ ፈርዖን ኺድ፡፡ እርሱ ወሰን አልፏልና፡፡
79|18|በለውም፡- «ወደ መጥራራትህ ላንተ (መንገድ) አለህን?»
79|19|«ወደ ጌታህም ልመራህ ትፈራውም ዘንድ፤ (መንገድ አለህን?)» አለው፡፡
79|20|ታላቂቱንም ተዓምር አሳየው፡፡
79|21|አስተባበለም፤ አመጸም፡፡
79|22|ከዚያም (ለማጥፋት) የሚተጋ ኾኖ ዞረ፡፡
79|23|(ሰራዊቶቹን) ሰበሰበም፤ ተጣራም፡፡
79|24|አለም፡- «እኔ ታላቁ ጌታችሁ ነኝ፡፡»
79|25|አላህም በኋለኛይቱና በፊተኛይቱ (ቃል) ቅጣት ያዘው፡፡
79|26|በዚህ ውስጥ ለሚፈራ ሰው በእርግጥ መገምገሚያ አለበት፡፡
79|27|ባፈጣጠር እናንተ ይበልጥ የበረታችሁ ናችሁን? ወይንስ ሰማይ? (አላህ) ገነባት፡፡
79|28|ከፍታዋን አጓነ፤ አስተካከላትም፡፡
79|29|ሌሊቷንም አጨለመ፡፡ ቀንዋንም ገለጸ፡፡
79|30|ምድርንም ከዚህ በኋላ ዘረጋት፡፡
79|31|ውሃዋንና ግጦሿን ከእርሷ አወጣ፡፡
79|32|ጋራዎችንም አደላደላቸው፡፡
79|33|ለእናንተና ለእንስሶቻችሁ መጣቀሚያ ይኾን ዘንድ (ይህን አደረገ)፡፡
79|34|ታላቂቱም መዐት በመጣች ጊዜ፣
79|35|ሰው ሁሉ የሠራውን በሚያስታውስበት ቀን፣
79|36|ገሀነምም ለሚያይ ሰው በተገለጠች ጊዜ፣
79|37|የካደ ሰውማ፣
79|38|ቅርቢቱንም ሕይወት የመረጠ፣
79|39|ገሀነም እርሷ በእርግጥ መኖሪያው ናት፡፡
79|40|በጌታው ፊት መቆምን የፈራ ሰውማ ነፍሱንም ከዝንባሌዋ የከለከለ
79|41|ገነት እርሷ በእርግጥ መኖሪያው ናት፡፡
79|42|«ከሰዓቲቱ መቼ ነው መኾኛዋ?» ሲሉ ይጠይቁሃል፡፡
79|43|አንተ እርሷን ከማስታወስ በምን ውስጥ ነህ?
79|44|(የዕውቀት) መጨረሻዋ ወደ ጌታህ ብቻ ነው፡፡
79|45|አንተ የሚፈራትን ሰው አስፈራሪ ብቻ ነህ፡፡
79|46|እነርሱ በሚያዩዋት ቀን ያንዲት ቀን ምሽትን ወይም ረፏዷን እንጅ ያልቆዩ ይመስላሉ፡፡

Pages ( 79 of 114 ): « Previous1 ... 7778 79 8081 ... 114Next »