Amharic Quran

15|1|አ.ለ.ረ (አሊፍ ላም ራ) ይህች (አናቅጽ) ከመጽሐፉ አንቀጾችና ገላጭ ከኾነው ቁርኣን ናት፡፡
15|2|እነዚያ የካዱት (በትንሣኤ ቀን) ሙስሊሞች በኾኑ ኖሩ በብዛት ይመኛሉ፡፡
15|3|ተዋቸው ይብሉ፤ ይጠቀሙም፡፡ ተስፋም ያዘናጋቸው፡፡ በእርግጥም (መጥፎ ፍጻሜያቸውን) ያውቃሉ፡፡
15|4|ማንኛይቱንም ከተማ ለእርሷ የተወሰነ መጽሐፍ (ጊዜያት) ያላት ኾና እንጂ አላጠፋንም፡፡
15|5|ማንኛይቱም ሕዝብ ጊዜዋን ምንም አትቀድምም፡፡ (ከእርሱ) አይቆዩምም፡፡
15|6|«አንተ ያ በእርሱ ላይ ቁርኣን የተወረደለት ሆይ! አንተ በእርግጥ ዕብድ ነህ» አሉም፡፡
15|7|«ከእውነተኞቹ እንደ ኾንክ በመላእክት (መስካሪ) ለምን አትመጣንም» (አሉ)፡፡
15|8|መላእክትን በእውነት (በቅጣት) እንጂ አናወርድም፡፡ ያን ጊዜም የሚቆዩ አይደሉም፡፡
15|9|እኛ ቁርኣንን እኛው አወረድነው፡፡ እኛም ለእርሱ ጠባቂዎቹ ነን፡፡
15|10|ከአንተም በፊት በነበሩት በመጀመሪያዎቹ ሕዝቦች ውስጥ (መልክተኞችን) በእርግጥ ልከናል፡፡
15|11|ማንኛውም መልእክተኛ በእርሱ የሚያላግጡበት ኾነው እንጅ አይመጣቸውም ነበር፡፡
15|12|እንደዚሁ (ማስተባበልን) በአመጸኞቹ ልቦች ውስጥ እናገባዋለን፡፡
15|13|በእርሱ አያምኑበትም፡፡ የቀድሞዎቹም ድርጊት በእርግጥ አልፋለች፤ (እንደጠፉ ይጠፋሉ)፡፡
15|14|በእነርሱም ላይ ከሰማይ ደጃፍን በከፈትንላቸውና በእርሱ ሲወጡ በዋሉ ኖሮ፤
15|15|«የተዘጉት ዓይኖቻችን ናቸው፡፡ እንዲያውም እኛ የተደገመብን ሰዎች ነን» ባሉ ነበር፡፡
15|16|በሰማይም ላይ ቡርጆችን በእርግጥ አድርገናል፡፡ ለተመልካቾችም (በከዋክብት) አጊጠናታል፡፡
15|17|ከተባረረ ሰይጣንም ሁሉ ጠብቀናታል፡፡
15|18|ግን (ወሬ) መስማትን የሚሰርቅ ወዲየውኑ አብሪ ችቦ ይከተለዋል፡፡ (ያቃጥለዋል)፡፡
15|19|ምድርንም ዘረጋናት፡፡ በውስጧም ኮረብታዎችን ጣልናባት፡፡ በውስጧም (የተለካን) በቃይ ሁሉ አበቀልንባት፡፡
15|20|በእርሷም ውስጥ ለእናንተ መኖሪያዎችንና ለእርሱ መጋቢዎቹ ያልኾናችሁትንም (እንስሳትን) አደረግንላችሁ፡፡
15|21|መካዚኖቹም (መክፈቻቸው) እኛ ዘንድ ያልሆነ ምንም ነገር የለም፡፡ በተወሰነም ልክ እንጂ አናወርደውም፡፡
15|22|ነፋሶችንም (ደመናን) ተሸካሚዎች አድርገን ላክን፡፡ ከሰማይም (ከደመና) ዝናብን አወረድን፡፡ እርሱንም አጠጣናችሁ፡፡ እናንተም ለእርሱ አድላቢዎች አይደላችሁም፡፡
15|23|እኛም ሕያው የምናደርግና የምንገድል እኛው ብቻ ነን፡፡ እኛም (ፍጡርን ሁሉ ) የምንወርስ (ቀሪ) ነን፡፡
15|24|ከእናንተም ተቀዳሚዎቹን በእርግጥ ዐውቀናል፡፡ ወደ ኋላም ቀሪዎቹን በእርግጥ ዐውቀናል፡፡
15|25|ጌታህም እርሱ ይሰበስባችኋል፡፡ እርሱ ጥበበኛ ዐዋቂ ነውና፡፡
15|26|ሰውንም ከሚቅጨለጨል ሸክላ ከሚገማ ጥቁር ጭቃ በእርግጥ ፈጠርነው፡፡
15|27|ጃንንም (ከሰው) በፊት ከእሳት ነበልባል ፈጠርነው፡፡
15|28|ጌታህም ለመላእክት ባለጊዜ (አስታውስ)፡፡ እኔ ሰውን ከሚቅጨለጨል ሸክላ ከሚገማ ጭቃ እፈጥራለሁ፡፡
15|29|(ፍጥረቱን) ባስተካከልኩትና በውስጡ ከመንፈሴ በነፋሁበትም ጊዜ ለእርሱ ሰጋጆች ኾናችሁ ውደቁ፡፡
15|30|መላእክትም መላውም ተሰብስበው ሰገዱ፡፡
15|31|ኢብሊስ (ዲያብሎስ) ብቻ ሲቀር፡፡ ከሰጋጆቹ ጋር ከመኾን እንቢ አለ፡፡
15|32|(አላህም) «ኢብሊስ ሆይ! ከሰጋጆቹ ጋር የማትኾን ላንተ ምን ምክንያት አለህ» አለው፡፡
15|33|«ከሚቅጨለጨል ሸክላ ከግም ጭቃ ለፈጠርከው ሰው ልሰግድ አይገባኝም» አለ፡፡
15|34|(አላህ) አለው «ከርሷም ውጣ፡፡ አንተ የተባረርክ እርጉም ነህና፡፡»
15|35|«ባንተ ላይም እስከ ፍርዱ ቀን ድረስ እርግማን አለብህ፡፡»
15|36|«ጌታዬ ሆይ! እንግዲውያስ (ሰዎች) እስከሚቀሰቀሱበት ቀን ድረስ አቆየኝ» አለ፡፡
15|37|(አላህም) አለ «አንተ ከሚቆዩት ነህ፡፡
15|38|«እስከታወቀው ወቅት ቀን ድረስ፡፡»
15|39|(ኢብሊስ) አለ «ጌታዬ ሆይ! እኔን በማጥመምህ ይኹንብኝ ለነርሱ በምድር ላይ (ኀጢአትን) እሸልምላቸዋለሁ፡፡ ሁሉንም አጠማቸዋለሁም፡፡»
15|40|«ከነርሱ ፍጹሞቹ ባሮችህ ብቻ ሲቀሩ፡፡»
15|41|(አላህም) አለ «ይህ በእኔ ላይ (መጠበቁ የተገባ) ቀጥተኛ መንገድ ነው፡፡»
15|42|«እነሆ ባሮቼ በእነሱ ላይ ላንተ ስልጣን የለህም፡፡ ከጠማሞቹ የተከተለህ ሰው ብቻ ሲቀር፡፡»
15|43|«ገሀነምም (ለርሱና ለተከተሉት) ለመላውም በእርግጥ ቀጠሯቸው ናት፡፡
15|44|«ለእርሷ ሰባት ደጃፎች አሏት፡፡ ለየደጀፉም ሁሉ ከእነሱ የተከፈለ ፋንታ አለ፡፡
15|45|«እነዚያ (ከኀጢአት) የተጠነቀቁት በአትክልቶችና በምንጮች ውስጥ ናቸው፡፡
15|46|«ጸጥተኞች ኾናችሁ በሰላም ግቧት (ይባላሉ)፡፡
15|47|«ባልጋዎችም ላይ ፊት ለፊት የሚቅጣጩ ወንድማማቾች ኾነው በደረቶቻቸው ውስጥ ከቂም ያለውን ሁሉ እናስወግዳለን፡፡
15|48|«በእርሷም ውስጥ ድካም አይነካቸውም፡፡ እነሱም ከእርሷ የሚወጡ አይደሉም፡፡»
15|49|ባሮቼን እኔ መሓሪው አዛኙ እኔው ብቻ መኾኔን ንገራቸው፡፡
15|50|ቅጣቴም እርሱ አሳማሚ ቅጣት መኾኑን (ንገራቸው)፡፡
15|51|ከኢብራሂም እንግዶችም (ወሬ) ንገራቸው፡፡
15|52|በእርሱ ላይ በገቡና ሰላም ባሉት ጊዜ የኾነውን (አስታውስ)፡፡ (እርሱም) «እኛ ከእናንተ ፈሪዎች ነን» አላቸው፡፡
15|53|«አትፍራ፤ እኛ ዐዋቂ በኾነ ወንድ ልጅ እናበስርሃለን» አሉት፡፡
15|54|«እርጅና የደረሰብኝ ከመኾኔ ጋር አበሰራችሁኝን በምን ታበስሩኛላችሁ» አለ፡፡
15|55|«በእውነት አበሰርንህ፡፡ ከተሰፋ ቆራጮችም አትኹን» አሉ፡፡
15|56|«ከጠማማዎችም በስተቀር ከጌታው እዝነት ተስፋን የሚቆርጥ ማነው» አለ፡፡
15|57|«እናንተ መልክተኞች ሆይ! ኧረ ለመኾኑ ነገራችሁ ምንድን ነው» አለ፡፡
15|58|«እኛ አመጸኞች ወደ ኾኑ ሕዝቦች ተልከናል» አሉት፡፡
15|59|«የሉጥ ቤተሰቦች ብቻ ሲቀሩ፡፡ (እነርሱን) እኛ ሁላቸውንም በእርግጥ የምናድናቸው ነን፡፡
15|60|«ሚስቱ ብቻ ስትቀር፡፡ እርሷን (በቅጣቱ ውስጥ) ከሚቀሩት መኾኗን ወሰነናል» (አሉ)፡፡
15|61|መልክተኞቹም የሉጥን ቤተሰቦች በመጡባቸው ጊዜ፤
15|62|(ሉጥ) «እናንተ የተሳታችሁ ሕዝቦች ናችሁ» አላቸው፡፡
15|63|«አይደለም እኛ ሕዝቦችህ በርሱ ይጠራጠሩበት በነበሩት ቅጣት መጣንህ» አሉት፡፡
15|64|«እውነትንም ይዘን መጣንህ፡፡ እኛም በእርግጥ እውነተኞች ነን፡፡
15|65|ከቤተሰብህም ጋር በሌሊቱ ከፊል ኺድ፡፡ ከኋላቸውም ተከተል፡፡ ከእናንተም አንድም ሰው ወደ ኋላው አይገላመጥ፡፡ ወደ ታዘዛችሁበትም ስፍራ እለፉ» (አሉት)፡፡
15|66|ወደርሱም ያንን ትእዛዝ አወረድን፡፡ (እርሱም) የእነዚህ (ሕዝቦች) መጨረሻ ያነጉ ሲኾኑ (ሥራቸው) መቆረጥ ነው፡፡
15|67|የከተማይቱም ሰዎች የሚበሳሰሩ ኾነው መጡ፡፡
15|68|(ሉጥም) አለ «እነዚህ እንግዶቼ ናቸውና አታጋልጡኝ፡፡
15|69|«አላህንም ፍሩ፤ አታሳፍሩኝም፡፡»
15|70|«ከዓለማት (ማንንም እንዳታስተናግድ) አልከለከልንህምን» አሉት፡፡
15|71|(ሉጥም) «እነኝህ ሴቶች ልጆቼ ናቸው፡፡ ሠሪዎች ብትኾኑ (አግቧቸው)» አለ፡፡
15|72|በዕድሜህ እንምላለን እነሱ በእርግጥ በስከራቸው ውስጥ ይዋልላሉ፡፡
15|73|ጩኸቲቱም ፀሐይ የወጣችባቸው ሲኾኑ ያዘቻቸው፡፡
15|74|ላይዋንም ከታችዋ አደረግን፡፡ በእነሱም ላይ የሸክላ ደንጊያዎችን አዘነብንባቸው፡፡
15|75|በዚህ ውስጥ ለተመልካቾች በእርግጥ መገምገሚያዎች አሉበት፡፡
15|76|እሷም (ከተማይቱ) በቀጥታ መንገድ ላይ ናት፡፡
15|77|በዚህ ውስጥ በእርግጥ ለምእምናን መገሰጫ አለ፡፡
15|78|እነሆ የአይከት ሰዎችም በእርግጥ በዳዮች ነበሩ፤
15|79|ከነሱም ተበቀልን ሁለቱም (የሉጥና የአይከት ሕዝቦች ከተሞች) በእርግጥ በግልጽ መንገድ ላይ ናቸው፡፡
15|80|የሒጅርም ሰዎች መልክተኞቹን በእርግጥ አስተባበሉ፡፡
15|81|ተዓምራታችንንም ሰጠናቸው፡፡ ከእርሷም ዘንጊዎች ነበሩ፡፡
15|82|ከኮረብታዎችም ቤቶችን ጸጥተኞች ኾነው ይጠርቡ ነበር፡፡
15|83|ያነጉም ሲኾኑ ጩኸት ያዘቻቸው፤ (ወደሙ)፡፡
15|84|ይሠሩትም የነበሩት ሕንጻ ምንም አልጠቀማቸውም፡፡
15|85|ሰማያትንና ምድርንም በመካከላቸው ያለውንም ሁሉ በእውነት እንጂ (በላግጣ) አልፈጠርንም፡፡ ሰዓቲቱም በእርግጥ መጪ ናት፡፡ መልካምንም ይቅርታ አድርግላቸው፡፡
15|86|ጌታህ እርሱ (ያልነበረን) ፈጣሪው ዐዋቂው ነው፡፡
15|87|ከሚደጋገሙ የኾኑን ሰባትንና ታላቁንም ቁርኣን (በሙሉ) በእርግጥ ሰጠንህ፡፡
15|88|ከእነርሱ (ከከሓዲዎች) ብዙዎችን ወገኖች በእርሱ ወደ አጣቀምንበት ጸጋ ዓይኖችህን አትዘርጋ፡፡ በእነሱም ላይ (ባያምኑ) አትዘን፡፡ ክንፍህንም ለምእምናን አለዝብ፡፡
15|89|በልም «እኔ ግልጽ አስፈራሪው እኔ ነኝ፡፡»
15|90|(ሰዎችን ለማገድ የመካን በሮች) በተከፋፈሉት ላይ እንደ አወረድነው (በኾነ ቅጣት አሰፈራሪያችሁ ነኝ በል)፡፡
15|91|(እነርሱም) እነዚያ ቁርኣንንን ክፍልፍሎች ያደረጉ ናቸው፡፡
15|92|በጌታህም እንምላለን፡፡ ሁላቸውንም እንጠይቃቸዋለን፤
15|93|ይሠሩት ከነበሩት ነገር ሁሉ፡፡
15|94|የታዘዝክበትንም ነገር በይፋ ግለጽ፡፡ አጋሪዎችንም ተዋቸው፡፡
15|95|ተሳላቂዎችን ሁሉ እኛ በቅተንሃል፡፡
15|96|(እነሱም) እነዚያ ከአላህ ጋር ሌላ አምላክን ያደረጉ ናቸው፡፡ በእርግጥም (ፍጻሜያቸውን) ወደፊት ያውቃሉ፡፡
15|97|አንተም በሚሉት ነገር ልብህ የሚጠብ መኾኑን በእርግጥ እናውቃለን፡፡
15|98|ጌታህንም ከማመስገን ጋር አጥራው ከሰጋጆቹም ኹን፡፡
15|99|እውነቱም (ሞት) እስኪመጣህ ድረስ ጌታህን ተገዛ፡፡

Pages ( 15 of 114 ): « Previous1 ... 1314 15 1617 ... 114Next »