Amharic Quran

36|1|የ.ሰ.(ያ ሲን)
36|2|ጥበብ በተመላበት ቁርኣን እምላለሁ፡፡
36|3|አንተ በእርግጥ ከመልክተኞቹ ነህ፡፡
36|4|በቀጥታም መንገድ ላይ ነህ፡፡
36|5|አሸናፊ አዛኝ ከሆነው አምላክ መወረድን ተወረደ፡፡
36|6|አባቶቻቸው ያልተስፈራሩትን ሕዝቦች ልታስጠነቅቅበት (ተወረደ)፡፡ እነርሱ ዘንጊዎች ናቸውና፡፡
36|7|በአብዛኞቻቸው ላይ ቃሉ በእውነት ተረጋገጠ፡፡ ስለዚህ እነርሱ አያምኑም፡፡
36|8|እኛ በአንገቶቻቸው ላይ እንዛዝላዎችን አደረግን፡፡ እርሷም (እንዛዝላይቱ) ወደ አገጮቻቸው ደራሽ ናት፡፡ እነርሱም ራሶቻቸውን ያንጋጠጡ ናቸው፡፡
36|9|ከስተፊታቸውም ግርዶን ከስተኋላቸውም ግርዶን አደረግን፡፡ ሸፈንናቸውም፡፡ ስለዚህ እነሱ አያዩም፡፡
36|10|ብታሰጠነቅቃቸውም ባታስጠነቅቃቸውም በእነርሱ ላይ እኩል ነው፡፡ አያምኑም፡፡
36|11|የምታስጠነቅቀው ግሳጼን የተከተለንና አልረሕማንን በሩቅ የፈራን ሰው ብቻ ነው፡፡ በምሕረትና በመልካም ምንዳም አብስረው፡፡
36|12|እኛ ሙታንን እኛ በእርግጥ ሕያው እናደርጋለን፡፡ ያስቀደሙትንም ሥራ ፈለጎቻቸውንም እንጽፋለን፡፡ ነገሩንም ሁሉ ገላጭ መሪ በኾነ መጽሐፍ ውስጥ አጠቃለልነው፡፡
36|13|ለእነርሱም የከተማይቱን (የአንጾኪያን) ሰዎች ምሳሌ መልክተኞቹ በመጧት ጊዜ (የኾነውን) ግለጽላቸው፡፡
36|14|ወደእነርሱ ሁለትን ሰዎች በላክንና ባስተባበሉዋቸው ጊዜ በሶስተኛም በአበረታንና እኛ ወደ እናንተ መልክተኞች ነን ባሏቸው ጊዜ (የኾነውን ምሳሌ ግለጽላቸው)፡፡
36|15|እናንተ መሰላችን ሰዎች እንጂ ሌላ አይደላችሁም፡፡ አልረሕማንም ምንም ነገር አላወረደም፡፡ እናንተ የምትዋሹ እንጂ ሌላ አይደላችሁም አሉዋቸው፡፡
36|16|(መልክተኞቹም) አሉ «ጌታችን ያውቃል፡፡ እኛ ወደእናንተ በእርግጥ መልክተኞች ነን፡፡
36|17|«በእኛ ላይም ግልጽ የኾነ ማድረስ እንጂ ሌላ የለብንም፡፡»
36|18|(ሕዝቦቹም) «እኛ በእናንተ ገደ ቢሶች ኾን፡፡ ባትከለከሉ በእርግጥ እንወግራችኋለን፡፡ ከእኛም አሳማሚ ቅጣት በእርግጥ ያገኛችኋል» አሉ፡፡
36|19|«ገደ ቢስነታችሁ ከእናንተው ጋር ነው፡፡ ብትገሰጹ (ትዝታላችሁን?) በእውነቱ እናንተ ወሰን አላፊዎች ሕዝቦች ናችሁ» አሏቸው፡፡
36|20|ከከተማይቱም ሩቅ ዳርቻ የሚሮጥ ሰው መጣ፡፡ «ወገኖቼ ሆይ! መልክተኞቹን ተከተሉ» አለ፡፡
36|21|«እነርሱ ቅኑን መንገድ የተመሩ ሲኾኑ ዋጋን የማየጠይቁዋችሁን ሰዎች ተከተሉ» (አላቸው)፡፡
36|22|«ያንንም የፈጠረኝን፤ ወደርሱም የምትመለሱበትን (ጌታ) የማልገዛ ለእኔ ምን አለኝ?» (አለ)፡፡
36|23|«ከእርሱ ሌላ አማልክትን እይዛለሁን? አልረህማን በጉዳት ቢሻኝ ምልጃቸው ከእኔ (ለመመለስ) ምንም አትጠቅመኝም፤ አያድኑኝምም፡፡
36|24|«እኔ ያን ጊዜ በግልጽ ስህተት ውስጥ ነኝ፡፡
36|25|«እኔ በጌታችሁ አመንኩ፤ ስሙኝም፤» (አለ)፡፡
36|26|«ገነትን ግባ» ተባለ፡፡ (እርሱም) አለ፡- «ወገኖቼ ቢያውቁ እመኛለሁ፡፡
36|27|«ጌታዬ ለእኔ ምሕረት ያደረገልኝና ከተከበሩትም ያደረገኝ መኾኑን፡፡»
36|28|ከእርሱም በኋላ በሕዝቦቹ ላይ (ልናጠፋቸው) ሰራዊትን ከሰማይ አላወረድንም፡፡ (በማንም ላይ) አወራጆችም አልነበርንም፡፡
36|29|(ቅጣታቸው) አንዲት ጩኸት እንጂ ሌላ አልነበረችም፡፡ ወዲያውኑም እነርሱ ጠፊዎች ኾኑ፡፡
36|30|በባሮቹ ላይ ዋ ቁልጭት! ከመልክተኛ አንድም አይመጣቸውም በእርሱ የሚሳለቁበት ቢኾኑ እንጅ፡፡
36|31|ከእነርሱ በፊት ከክፍለ ዘመናት ሕዝቦች ብዙዎችን ማጥፋታችንንና እነርሱ ወደነርሱ የማይመለሱ መኾናቸውን አላወቁምን?
36|32|ሁሉም እኛ ዘንድ የሚሰበሰቡ የሚቀረቡ እንጂ ሌላ አይደሉም፡፡
36|33|የሞተችውም ምድር ለእነርሱ ምልክት ናት! ሕያው አደረግናት፡፡ ከእርሷም ፍሬን አወጣን፤ ከርሱም ይበላሉ፡፡
36|34|በእርሷም ውሰጥ ከዘምበባዎችና ከወይኖች የኾኑ አትክልቶችን አደረግን፡፡ በእርሷም ውስጥ ምንጮችን አፈለቅን፡፡
36|35|ከፍሬውና እጆቻቸው ከሠሩትም ይበሉ ዘንድ (ይህን አደረግን)፤ አያመሰግኑምን?
36|36|ያ ምድር ከምታበቅለው ከነፍሶቻቸውም ከማያውቁትም ነገር ዓይነቶችን ሁሏንም የፈጠረ (አምላክ) ጥራት ይገባው፡፡
36|37|ሌሊቱም ለእነርሱ ምልክት ነው፡፡ ከእርሱ ላይ ቀንን እንገፍፋለን፡፡ ወዲያውኑም እነርሱ በጨለማ ውስጥ ይገባሉ፡፡
36|38|ፀሐይም ለእርሷ ወደ ሆነው መርጊያ ትሮጣለች፡፡ ይህ የአሸናፊው የዐዋቂው አምላክ ውሳኔ ነው፡፡
36|39|ጨረቃንም የመስፈሪያዎች ባለቤት ሲኾን እንደ ዘንባባ አሮጌ ቀንዘል እስኪኾን ድረስ (መኼዱን) ለካነው፡፡
36|40|ፀሐይ ጨረቃን ልትደርስበት አይገባትም፡፡ ሌሊትም ቀንን (ያለ ጊዜው) ቀዳሚ አይኾንም፡፡ ሁሉም በመዞሪያቸው ውስጥ ይዋኛሉ፡፡
36|41|እኛም (የቀድሞ) ትውልዳቸውን በተሞላች መርከብ ውስጥ የጫን መኾናችን ለእነርሱ ምልክት ነው፡፡
36|42|ከመሰሉም በእርሱ የሚሳፈሩበትን ለእነርሱ ፈጠርንላቸው፡፡
36|43|ብንሻም እናሰጥማቸዋለን፡፡ ለእነርሱም ረዳት የላቸውም፡፡ እነርሱም የሚድዳኑ አይደሉም፡፡
36|44|ግን ከእኛ ለኾነው ችሮታና እስከ ጊዜ ሞታቸው ለማጣቀም (አዳንናቸው)፡፡
36|45|ለእነርሱም «በስተፊታችሁና በኋለችሁ ያለውን ነገር ተጠንቀቁ ይታዘንላችኋልና» በተባሉ ጊዜ (ፊታቸውን ያዞራሉ)፡፡
36|46|ከጌታቸውም ተዓምራት ማንኛይቱም ተዓምር አትመጣላቸውም፤ ከእርሷ የሚሸሹ ቢኾኑ እንጅ፡፡
36|47|ለእነርሱም «አላህ ከሰጣችሁ ሲሳይ ለግሱ» በተባሉ ጊዜ እነዚያ የካዱት ለእነዚያ ላመኑት «አላህ ቢሻ ኖሮ የሚያበላውን ሰው እናበላለን? እናንተ በግልጽ ስህተት ውስጥ እንጂ በሌላ ላይ አይደላችሁም» ይላሉ፡፡
36|48|«እውነተኞችም እንደኾናችሁ ይህ ቀጠሮ መቼ ነው?» ይላሉ፡፡
36|49|እነርሱ የሚከራከሩ ሲኾኑ በድንገት የምትይዛቸው የኾነችን አንዲትን ጩኸት እንጂ ሌላን አይጠባበቁም፡፡
36|50|(ያን ጊዜ) መናዘዝንም አይችሉም፡፡ ወደ ቤተሰቦቻቸወም አይመለሱም፡፡
36|51|በቀንዱም ይነፋል፡፡ ወዲያውኑም እነርሱ ከመቃብሮቻቸው ወደ ጌታቸው በፍጥነት ይገሰግሳሉ፡፡
36|52|«ወይ ጥፋታችን! ከመኝታችን ማን ቀሰቀሰን? ይህ ያ አዛኙ ጌታ (በእርሱ) የቀጠረን መልክተኞቹም እውነትን የነገሩን ነው» ይላሉ፡፡
36|53|(እርሷ) አንዲት ጩኸት እንጂ አይደለችም፡፡ ወዲያውኑም እነርሱ እኛ ዘንድ የሚሰበሰቡ የሚቀርቡ ናቸው፡፡
36|54|«ዛሬም ማንኛይቱም ነፍስ ምንም አትበደልም፡፡ ትሠሩትም የነበራችሁትን እንጂ ሌላን አትመነዱም» (ይባላሉ)፡፡
36|55|የገነት ሰዎች ዛሬ በእርግጥ በሥራዎች ውስጥ ተደሳቾች ናቸው፡፡
36|56|እነርሱም ሚስቶቻቸውም በጥላዎች ውስጥ ናቸው፡፡ ባለ አጎበር አልጋዎች ላይ ተደጋፊዎች ናቸው፡፡
36|57|በውስጧ ለእነርሱ ፍራፍሬዎች አሏቸው፡፡ ለእነርሱም የሚፈልጉት ሁሉ አልላቸው፡፡
36|58|(ለእነርሱም) አዛኝ ከሆነው ጌታ በቃል ሰላምታ አላቸው።
36|59|(ይላልም) «እናንተ አመጸኞች ሆይ! ዛሬ (ከምእምናን) ተለዩ፡፡»
36|60|የአደም ልጆች ሆይ! ሰይጣንን አትገዙ፤ እርሱ ለእናንተ ግልጽ ጠላት ነውና በማለት ወደእናንተ አላዘዝኩምን?
36|61|ተገዙኝም፤ ይህ ቀጥተኘ መንገድ ነው፤ (በማለትም)፡፡
36|62|ከእናንተም ብዙን ፍጡር በእርግጥ አሳስቷል፡፡ የምታውቁም አልነበራችሁምን?
36|63|ይህቺ ያቺ ትቀጠሩዋት የነበረችው ገሀነም ናት፡፡
36|64|ትክዱ በነበራችሁት ምክንያት ዛሬ ግቧት (ይባላሉ)፡፡
36|65|ዛሬ በአፎቻቸው ላይ እናትምና እጆቻቸው ያነጋግሩናል፡፡ እግሮቻቸውም ይሠሩት በነበሩት ሁሉ ይመሰክራሉ፡፡
36|66|ብንሻም ኖሮ በዐይኖቻቸው ላይ በአበስን ነበር፡፡ መንገድንም (እንደ ልመዳቸው) በተሽቀዳደሙ ነበር፡፡ እንዴትም ያያሉ?
36|67|ብንሻም ኖሮ በስፍራቸው ላይ እንዳሉ ወደ ሌላ ፍጥረት በለወጠናቸው ነበር፡፡ መኼድንም መመለስንም ባልቻሉም ነበር፡፡
36|68|ዕድሜውንም የምናረዝመውን ሰው በፍጥረቱ (ወደ ደካማነት) እንመልሰዋለን፤ አያውቁምን?
36|69|(ሙሐመድን) ቅኔንም አላስተማርነውም፡፡ ለእርሱም አይግገባውም፡፡ እርሱ (መጽሐፉ) መገሰጫና ገላጭ ቁርኣን እንጅ (ቅኔ) አይደለም፡፡
36|70|(ግሣጼነቱም ልቡ) ሕያው የኾነን ሰው ሊያስፈራራበትና ቃሉም በከሓዲዎች ላይ ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡
36|71|እኛ እጆቻችን (ኃይሎቻችን) ከሠሩት ለእነርሱ እንስሳዎችን መፍጠራችንን አያውቁምን? እነርሱም ለእርሷ ባለ መብቶች ናቸው፡፡
36|72|ለእነርሱም ገራናት፡፡ ስለዚህ ከእርሷ ውስጥ የሚጋልቡት አልለ፡፡ ከእርሷም ይበላሉ፡፡
36|73|ለእነርሱም በእርሷ ውስጥ (ሌሎች) ጥቅሞች መጠጦችም አሉዋቸው፡፡ ታዲያ አያመሰግኑምን;
36|74|መረዳትንም በመከጀል ከአላህ ሌላ አማልክትን ያዙ፡፡
36|75|መርዳታቸውን አይችሉም፡፡ እነርሱም ለእርሳቸው (ወደ እሳት) የተቀረቡ ሰራዊት ናቸው፡፡
36|76|ንግግራቸውም አያሳዝንህ፡፡ እኛ የሚደብቁትንም የሚገልጹትንም እናውቃለንና፡፡
36|77|ሰውየው እኛ ከፍቶት ጠብታ የፈጠርነው መኾናችን አላወቀምን? ወዲያውም እርሱ (ትንሣኤን በመካድ) ግልጽ ተከራካሪ ይኾናልን?
36|78|ለእኛም ምሳሌን አደረገልን፡፡ መፈጠሩንም ረሳ፡፡ «አጥንቶችን እነርሱ የበሰበሱ ሲኾኑ ሕያው የሚያደርጋቸው ማነው?» አለ፡፡
36|79|«ያ በመጀመሪያ ጊዜ (ከኢምንት) ያስገኛት ሕያው ያደርጋታል፡፡ እርሱም በፍጡሩ ሁሉ (ኹኔታ) ዐዋቂ ነው» በለው፡፡
36|80|ያ ለእናንተ በእርጥብ ዛፍ እሳትን ያደረገላችሁ ነው፡፡ ወዲያውኑም እናንተ ከእርሱ ታቀጣጥላላችሁ፡፡
36|81|ያ ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ ብጤያቸውን በመፍጠር ላይ ቻይ አይደለምን? ነው እንጅ፡፡ እርሱም በብዙ ፈጣሪው ዐዋቂው ነው፡፡
36|82|ነገሩም አንዳችን በሻ ጊዜ ኹን ማለት ነው፡፡ ወዲያው ይኾናልም፡፡
36|83|ያ የነገሩ ሁሉ ስልጣን በእጁ የኾነው ጌታ ጥራት ይገባው፡፡ ወደእርሱም ትመለሳላችሁ፡፡

Pages ( 36 of 114 ): « Previous1 ... 3435 36 3738 ... 114Next »